የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው - ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው - ዶክተር አለሙ ስሜ
አሰላ፤ መጋቢት 1/2016(ኢዜአ)፡- አሽከርካሪነት ስነ-ምግባር የሚጠይቅ ትልቅ ሙያ በመሆኑ የማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ አስገነዘቡ።
8ኛው የኦሮሚያ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎትና የትራፊክ ደህንነት ሳምንት በክልል ደረጃ በአሰላ ከተማ ተጀምሯል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በፕሮግራሙ ላይ እንደገለፁት የትራፊክ አደጋ መቆጣጠር እየተቻለን ችግር እያደረሰ ያለ ክስተት ነው ብለዋል።
ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው አደጋ በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስና በተሽከርካሪ ቴክኒክ ችግር የሚከሰት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በዚህ ላይ ትኩረታችን መጠናከር እንዳለበት አመላካች ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የትራፊክ አደጋ በየደረጃው በሚገኘው አመራርና የዘርፉ አካላት ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
አሽከርካሪነት ስነ-ምግባርና ትልቅ ሃላፊነትን የሚጠይቅ ሙያ ቢሆንም በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት በኩል በሚታይው ህገ-ወጥ አሰራርና ተግባራት በዘርፉ ሰልጥነው የሚወጡ ሙያተኞች ተገቢውን ክህሎት፣ ስነ ምግባርና ሃላፊነት ታጥቀው እየወጡ አይደለም ብለዋል።
በዚህም አደጋው በሁሉም የእድሜ ክልል ያለውን ትውልድ ህይወት እየቀጠፈና አያሌ ንብረት እያወደመ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትራፊክ አደጋን በጋራ መግታት ካልቻልን ነገ ሁሉም ቤት ሊገባ የሚችል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በመሆኑም መላው ህብረተሰብና የአመራር አካላት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት አለብን ነው ያሉት።
ከወንበር በላይ ሰውን በሰው ላይ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈልና ተሳፋሪዎችን ማጉላላት በዘርፉ በስፋት የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በመናህሪያዎች አካባቢ የሚታዩ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
መንግሥት ችግሮቹን ለመፍታት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በትራንስፖርት መናህሪያዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ ዲጂታል አገልግሎቶችን በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዘርፉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋትና ጠንካራ ህጎችን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ዓለሙ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መድን አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ በበኩላቸው ለትራፊክ አደጋ ምንጩ ከአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ጀምሮ መሆኑን አንስተዋል።
በሙያቸው ብቁ ያልሆኑ፣ ሃላፊነት የማይሰማቸውና የስነ-ምግባር ጉድለት የሚስተዋልባቸውን አሽከርካሪዎች ያለ በቂ ክህሎትና ዕውቀት ማውጣታቸውን እንደአብነት ጠቅሰዋል።
የማሰልጠኛ ተቋማት በዚህ መልኩ መቀጠል አይችሉም ያሉት አቶ ጀማል፤ መንግስት ተቋማቱ ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት የታጠቀ የሰው ሃይል ማፍራት እንዲችሉ የጥራት መለኪያ ስታንዳርድ እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራፊክ አደጋው በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጄንሲ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት ናቸው።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልን ጨምሮ ተቆጣጣሪ አካላት ይሄንን አስከፊ ችግር ለመቆጣጠርና አደጋውን ለመቀነስ በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
በተጨማሪም ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን በማስፋፋት ህብረተሰቡ ጤናውን ለመጠበቅና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
በኦሮሚያ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎትና የትራፊክ ደህንነት ሳምንት ስለ መንገድ ትራፊክ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻዎችና የህዝብ ቅስቀሳዎች እንደሚከናወኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የሞተር አልባ የመንገድ ጉዞዎችም የመርሃ ግብሩ አካል መሆናቸው ታውቋል።
በፕሮግራሙ ላይ ከአርሲ ዞንና አሰላ ከተማ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችና በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ተሳትፈዋል።