ቀጥታ፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ ታላቁን የዐብይ ፆም ሲፆም የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ እና ያለውን በማካፈል ሊሆን ይገባል - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2016(ኢዜአ)፡- ሕዝበ ክርስቲያኑ የዐብይ ፆም ወራትን የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ እና በጎ ምግባራትን በማከናወን ሊያሳልፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ የሚጀምረውን የዐብይ ፆምን በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ጾም ኃጢአትንና ዲያብሎስን እንዴት እንደሚያሸንፍ ጌታችን እኛን ያስተማረበት ነው ሲሉ መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ፆም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም በዐብይ ፆም ወራት በጎ ምግባራትን በማከናወን በተግባር ሊተረጉመው ይገባል ብለዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ ታላቁን የዐብይ ፆም ሲፆም በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ እና ያለውን በማካፈል ሊሆን እንሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም