ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም በአድዋ ድል መታሰቢያ የተሞክሮ ማዕከል ከፈተ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞቹ ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂዎች የሚጎበኙበትና በተግባር የሚሞክሩበት ማዕከል በአድዋ ድል መታሰቢያ ከፈተ። 

ማዕከሉ የግለሰብና የድርጅት ደንበኞች ምርትና አገልግሎቶችን የሚመለከቱበት፣ አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በተግባር በመሞከር የፈጠራ ሥራቸውን የሚያነሳሱበትና የቴክኖሎጂ ግኝቶችን የሚመራመሩበት መሆኑ ተመላክቷል።    

ማዕከሉ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ያለፈባቸውን በርካታ ሂደቶች የሚዘክርና አሁን ላይ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳይ እንዲሁም የወደፊቱን የቴክኖሎጂ እድገት የሚያመላክት መሆኑንም እንዲሁ።   


 

የኢትዮ ቴሌኮምን የዕድገት ደረጃዎች የሚተርኩና የሚያስቃኙ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ጨምሮ አሁን የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ልህቀት በሚያሳይ መልክ መደራጀቱንም ተጠቅሷል።  

ዘመኑ ያፈራቸውን የተለያዩ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን ለአብነትም እጅግ ፈጣን የ5ጂ ኮኔክቲቪቲ ቨርቹዋል ሪያሊቲ፣ የፈጠራ ሶሉሽኖችን፣ የስማርት ሆም አውቶሜሽን፤ የቴሌብር ፋይናንሺያል ግብይቶችንና የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ትስስርን ማካተቱ ተገልጿል።   

ስማርት የቱሪዝም አገልግሎቶችን፣ የርቀት ታካሚ ክትትልን፣ የስማርት ግብርና ቴክኒኮችን፣ ስማርት የትምህርትና የትምህርት መሳሪያዎችን፤ ስማርት የማዕድን ልማትን፣ የክላውድና የዳታ ማዕከል ሶሉሽንስ፣ ፈጣንና ሙሉ ጊዜ የደህንነት ቁጥጥር ሶሉሽን እንዲሁም በመዝናኛው ዘርፍ በ5 ጂ የታገዘ የሙዚቃ መዝናኛ ሶሉሽንንና በመሳሰሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተሞላ ማዕከል ነው ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም