በመንግሥትና የግል አጋርነት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥትና የግል አጋርነት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦በመንግሥትና የግል አጋርነት የመዲናዋን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በ450 ሚሊየን አሜሪካን ዶላር የሚገነባውን ምዕራፍ ሁለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሠራተኞች የ5 ሺህ የመኖሪያ ቤት የግንባታ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ የመኖሪያ ቤት የማግኘት ፍላጎት የመዲናዋ ነዋሪዎች የመጀመሪያ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።
የመዲናዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ምላሽ ለመስጠትም አልሚዎችን ማሳተፍ የሚያስችል በሕግና ፖሊሲ የተደገፈ አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የመንግሥትና የግል አጋርነትና የግል ቤት አልሚዎች በራሳቸው መንገድ ማልማት የሚችሉበት ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሠራተኞቻቸው የመኖሪያ ቤት መገንባት ለሚችሉ ተቋማትም መሬት በማቅረብ መገንባትና ማስገንባት እንዲችሉ እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መለያና ምልክት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማነትም ትጉህ ሠራተኞች ስላሉት መሆኑን ገልጸዋል።
ለአየር መንገዱ ሠራተኞች እንዲውል የተጀመረው የመኖሪያ ቤት ግንባታም በተያዘለት የጊዜ ገደብና በጀት እንዲጠናቀቅም ኮንትራቱን የወሰዱ ተቋማት በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ከተማ አስተዳደሩም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የአየር መንገዱ ሠራተኞች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ ፕሮጀክቱ በ450 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በጀት በሰንሻይን ኮንስትራክሽንና በቻይናው ሲ.ሲ.ሲ.ሲ የግንባታ ኩባንያ ይከናወናል ብለዋል።
በምዕራፍ ሁለት የሚገነባው ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤት የአየር መንገዱን ሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላት ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲከውኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የሠራተኞች የቤት ጥያቄ እንዲመለስ መደረጉም ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማነት በማስቀጠል የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ብለዋል።
የአየር መንገዱ ሠራተኞች የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ሥርዓት መዘርጋቱም አዳዲስ ሠራተኞችም ተቋሙን እንዲቀላቀሉ ጉጉት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ሳሙኤል ታፈሠ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚያስገነባቸው 5 ሺህ ቤቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
የኮንትራት ውል የወሰዱባቸውን የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችም በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ የሚያስችል የግንባታ ግብዓት በማስገባት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜናም ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላለፉት 35 ዓመታት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሳለፋቸውን ዘመናት በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅትም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰንሻይን ኮንስትራክሽን አክሲዮን ማኅበር አማካኝነት 3 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ላይ የተገነቡ 5 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችን መርቀዋል።
በክብረ በዓሉ ላይም በተቋሙ ረጅም ዓመታትን በታማኝነት ላገለገሉ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤትና ሌሎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።