የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚሰጠውን ግዳጆች በጀግንነትና በፍጹም ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር እየተወጣ ነው - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚሰጠውን ግዳጆች በጀግንነትና በፍጹም ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር እየተወጣ ነው - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚሰጠውን ግዳጆች በጀግንነትና በፍጹም ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር በማከናወን የአገርን ዕድገት በማጽናት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በተለያዩ ፖሊሳዊ ግዳጆች የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ አመራሮችና አባላት የእውቅናና የሽልማት መርኃ ግብር ተካሂዷል።
እውቅናና ሽልማቱ ፖሊሳዊ ግዳጆችን በአገር ፍቅር ስሜትና ጀግንነት ለተወጡ አመራሮችና አባላት የተሰጠ ሲሆን የገንዘብ ሽልማት፣ የማዕረግ ዕድገትና የሰርተፊኬት እውቅና ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አገሪቷን ከየትኛውም የወንጀል፣ የሽብርና የጽንፈኝነት ተግባር መጠበቅ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።
ተቋሙ በትጥቅ፣ በሥምሪት አቅምና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅሙ ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል።
ከ894 በላይ አገራዊ ትላልቅ ልማቶችንና ተቋማትን በኃላፊነት በመጠበቅ የአገርን ዕድገት በማጽናት ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑንም ጠቁመው እውቅና ላገኙት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተሻለ ፕሮፌሽናል ተቋም እንዲሆን የለውጥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው በመፈጸም አቅም ከአገር አልፎ ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
በወንጀል መከላከል አቅምም እየተከናወኑ የሚገኙት አኩሪ ሥራዎች ይበልጥ በማጠናከር ወደ ተሟላ ደረጃ በማድረስ የበቃ፣ የተደራጀ ሁሉንም ተልዕኮ በብቃት መፈጸም የሚችል ሰራዊት ለመገንባት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኢትዮጵያን በሚመስል መልኩ መደራጀቱን ገልጸዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የተሰጠውን አገራዊ ግዳጅ በጀግንነት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ሕገ-መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠው መብት እንዳይሸራረፍ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ለተሰለፉበት የሙያ መስክ ክብር የሚሰጡ፣ ተልዕኮዎቻቸውን በብቃት የሚወጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው ብለዋል።
እውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው የሰራዊቱ አባላት ለፈጸሙት ጀግንነት እውቅናና ሽልማት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
እውቅናው በቀጣይም የተሰጣቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ የሚያስችላቸውን የሞራል ስንቅ ያገኙበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የሚሰጣቸውን አገራዊ ግዳጆችን በፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር፣ በሰብዓዊነትና በጀግንነት ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው መርኃ ግብር የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።