በተለያዩ ተቋማት ለሚሰሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚደረገው ሙያዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ተቋማት ለሚሰሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚደረገው ሙያዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት ለሚሰሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚያደርገውን ሙያዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ሙያ ላይ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
ሥልጠናውን ከወሰዱ ባለሙያዎች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙትና ኮሙኒኬሽን ማኔጀር አቶ ፍስኃ ጌታቸው፤ ተቋሙ ለሕዝብ ግንኙት ባለሙያዎች እየሰጠ ያለው ሥልጠና ዘርፉን በተሻለ አቅም ለመምራት ያስችላል ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ተቋሙ ለተከታታይ ቀናት በቴሌቪዥንና ሬዲዮ ፕሮዳክሽንን ጨምሮ በምስል ቀረጻና ተያያዥ ዘርፎች የሰጠው ሥልጠና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተናቦ ለመሥራትና ወቅቱ የሚጠይቀውን ክህሎት ለማግኘት እድል እንደሰጣቸው ጠቅሰዋል።
በሥልጠናው ተግባርን ከንድፈ ሐሳብ ያቆራኘ ክህሎት እንዳስጨበጣቸው የገለጹት አቶ ፍስኃ በዘርፉ የተሻለና ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ግዛቸው አበረ በበኩሉ ሥልጠናው ተቋማት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተናበው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ክህሎት እንደሚያስጨብጣቸው ተናግሯል ።
በተለይም ዘመናዊ የሆነውን ሚዲያ ባህሪና አስፈላጊውን ክህሎት እንድናውቅ አድርጎናል ነው ያለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ በበኩላቸው ሥልጠናው ባለሙያዎች ያላቸውን ክህሎት ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል።
ሠልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን ልምድ፣ ተሞክሮና እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ የተቋማቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም ፍሬያማ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት ለሚሰሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚያደርገውን ሙያዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።