በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ ነው  - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ላስካ ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉትን የልማት አቅሞች አሟጦ በመጠቀም የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ከባስኬቶ ዞን ከተወጣጡ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና መልካም አስተዳድር ዙሪያ በላስካ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ ጊዜ የዞኑ ነዋሪዎች የተለያዩ መሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን በርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት የክልሉ መንግስት ያሉትን አቅሞች በመጠቀም የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ የመዋቅር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ከመፍታት ጀምሮ በክልሉ ያሉ የግብርናና ቱሪዝም ሀብቶችን እንዲሁም ሌሎች ሀብቶችን በመጠቀም ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተቀናጀ መንገድ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የዞኑን የአደረጃጀት ጥያቄ ከመመለስም ባለፈ የኮይሻ ግድብን ተከትሎ በተገነባው መንገድ የባስኬቶና አካባቢው ህዝብ ተጠቃሚነት ማደጉን አንስተዋል።

በቀጣይም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱትን የመንገድና የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ጥያቄዎችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳደሩ ገለጻ የዞኑ ህዝብ በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ ትጋቱን ማጠናከር አለበት።

በውይይቱ ላይ የባስኬቶ ዞን የሃይማኖት አባት ተዘራ መኮንን፣ መንግስት በዞኑ ሰፊ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ በመሆኑ የህዝቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

አሁንም በዞኑ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር መኖሩን ጠቅሰው ህብረተሰቡ ምርቱን በመሸጥ ተገቢውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ አዳጋች ከመሆኑም በላይ በህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ በመሆኑ መንግስት ለህዝቡ ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በባስኬቶ ዞን ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መኖሩንና ይህም መፍትሄ እንዲያገኝ ያነሱት ደግሞ ኢንጅነር ሚልኪያስ ደሮ ናቸው።

አቶ ዓለምብርሃን ካሣሁን በበኩላቸው በዞኑ ከሰላምና የፀጥታ ጋር የተያያዙ ችገሮች መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዞኑ እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የጎበኙ ሲሆን የላስካ ጤና ጣቢያ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ የዞኑን አስተዳደር ህንጻ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በላስካ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ መንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም