የኢትዮጵያ የባህር በርን ማግኘት በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት ያጎለብታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በርን ማግኘት በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት ያጎለብታል
ጅግጅጋ ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮዽያ የባህር በር ማግኘት በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነትንና የንግድ ትስስርን እንደሚያጎለብት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር በሽር አብዱላሂ ገለጹ።
በባህር በር አጠቃቀም ላይ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት ዛሬ በጅግጅጋ ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት ዶክተር በሽር አብዱላሂ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የባህር በር ማግኘት የቀጣናውን የንግድ ትስስር በማሳለጥ በኩል ሚናው የጎላ ነው።
የቀጣናው አገሮች በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ "በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው" ሲሉም አመልክተዋል።
በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ የሚያጋጥመውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም የባህር በር ማግኘት ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት በምስራቅ አገሪቷ ክፍልም ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያዳብርና የህዝቡን ተጠቃሚነት እንደሚያጎለብትም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያጎናፅፈውን የባህር በር ጉዳይ በዲፕሎማሲም ሆነ በምርምር ስራዎች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ተመራማሪ፣ የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳይ ዳይሪክተር ጀነራል ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስችሏት በርካታ ምክንያቶች እንዳሏት ጠቅሰዋል።
ጂኦ-ፖለቲካል፣ ተፈጥሮ፣ ታሪካዊ እውነታና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ዓለም አቀፍ ህጎችና የደህንነት ጉዳይ ከምክንያቶቿ ይጠቀሳሉ ብለዋል።
የባህር በር ያላቸውና የሌላቸው አገራት በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነታቸው እኩል አለመሆኑን አመልክተው፤ "ኢትዮጵያ የባህር በርን ለማግኘት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እድሎቿን እንድትጠቀም ምሁራን የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል" ብለዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ የባህር በርን ማግኘት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ የሚያጋጥመውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም የባህር በርን የማግኘት ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የሃያላን አገራትን ትኩረት የሳበ መሆኑን የገለጹት ጥናት አቅራቢው፤ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑ በራሱ ሌላኛው አመክንዮ እንደሆነ አስረድተዋል።
የባህር በር ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ መሞገት የሚያስችል ሰነድ ማዘጋጀት፣ ጥያቄውን ግልጽ ማድረግና ጉዳዩን ህዝባዊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ሁሉን አቀፍ ድርድርና ዲፕሎማሲ፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ድርጅቶችን መጠቀም፣ የሃይል ምንጭ ሽያጭን እንደ መደራደሪያ መጠቀምና ከፍተኛ የምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ የባህር በር የማግኘት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ መጻኢ እድል ጉዳይ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አብዱላሂ ናቸው።
የባህር በር ማግኘት ለቀጣይ ትውልድ "እዳ ሳይሆን ምንዳን" የምናወርስበት እንዲሁም ኢንቨስትመንትንና የወጪና ገቢ ምርትን በማሳለጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የዩኒቨርስቲ ምሁራንም "መንግስት የባህር በር ለማግኘትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያከናውነው ስራ ላይ ሚናችንን ማጎልበት ይጠቅብናል" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እና የመልካ-ፖለቲካዊ አንድምታ" በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት የዩኒቨርሲቲው ምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።