ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን እና ጂቡቲን ግንኙነት በይበልጥ ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው-አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ እና ጂቡቲን ግንኙነት እና ትብብር በይበልጥ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ብልጽግና ፓርቲም የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ፣ የደኅንነት፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ግንኙነት በዓርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን እንደሚገነዘብም ጠቅሰዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በጅቡቲው RPP ፓርቲ 45ኛ አመት የምስረታ በአል ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የ RPP ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ እስማኤል ኡማር ጊሌ እና የጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት የተከበሩ አ/ቃድር ካሚል መሐመድ የ RPP ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የጅቡቲ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር የ RPP ፓርቲ ዋና ጸሐፊ እና የጅቡቲ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስትር ሚስተር ኢሊያስ ሙሴ ዳዋሌ የ RPP አመራር እና አባላት፣ የክብር እንግዶች

ክቡራትና ክቡራን

ብልጽግና ፓርቲን በመወከል የRPP ፓርቲ 45ኛ የምስረታ በዓል ላይ መገኘቴ ትልቅ ክብር ነው እና የ RPP ፓርቲ 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ። በእኩልነት፣ በፍትህ፣ በመከባበር እና በብልጽግና ላይ የተመሰረተ የብልጽግና ፓርቲን በኢትዮጵያ ውስጥ የምንወክል ልዑካን ነን።

በዚህ በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ እንድንሳተፍ ስለጋበዙን እናመሰግናለን። በክብር እና በወንድማማችነት ለልዑካኖቻችን ላደረጋችሁት መልካም አቀባበልም እናመሰግናለን።

የተከበሩ ፕሬዝዳንት፣ክቡራን እና ክብራት

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ሞቅ ያለ ሰላምታዬን እና የእንኳን አደረሳችሁን እንድትቀበሉ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

የተከበሩ ፕሬዝዳንት

ክቡራን እና ክብራት

ከRPP ታሪክ እንደምንረዳው ያለፉት 45 ዓመታት ከጎረቤት ሀገራትና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለእድገት፣ ለሰላም፣ ለህዝቦች አንድነት፣ አብሮነት እና ትብብር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ወቅት ነው።

በፕሬዚዳንት ኢስማኢል የሚመራው የጅቡቲ አመራር ያላሰለሰ ጥረት ውጤት እያሳየ መሆኑን እና ጅቡቲን ጠቃሚ የንግድ ማዕከል እንድትሆን፣ የመረጋጋት ምሳሌ እና የእድገት ጎዳና እንድትሆን እንዳደረጋት በልበ ሙሉነት እንመሰክራለን።

በጅቡቲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር ለአፍሪካ ቀንድ ውህደት እና የጋራ ተጠቃሚነት የተሰሩ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እናደንቃለን። በአበይትነት ጅቡቲንና ኢትዮጵያን የሚያገናኙት ወደቦች፣ የባቡር መስመር እና አውራ ጎዳናዎች መጥቀስ ይቻላል።

የተከበሩ ፕሬዝዳንት

ክቡራን እና ኩቡራት

በአሁኑ ወቅት ከ14 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ብልጽግና ፓርቲ ለጎረቤት ሀገራት በዲፕሎማሲ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና በአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች መካከል ያለውን ውህደት እና የጋራ ተጠቃሚነት ለማጠናከር በፕሮግራሙ ላይ በግልፅ አስቀምጧል። ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ ቀንድ ጥቅሞች እርስ በርስ የተያያዙ እና የማይነጣጠሉ ናቸው።

ትብብራቸውም የተቀደሰ ነው ብሎ ያምናል። ብልጽግና ፓርቲ ለጅቡቲ ጠቃሚ የሆነው ለኢትዮጵያም ሆነ ለሶማሊያ አስፈላጊ እንደሆነ ለጎረቤት አገሮች ጠቃሚ የሆነው ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። የኢትዮጵያ ጥቅም ለሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ ይገነዘባል።

በተለይ ብልጽግና ፓርቲ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ድጋፍና ቀልጣፋ አገልግሎት እውቅና ይሰጣል። ብልጽግና ፓርቲ የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ደህንነት፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ግንኙነት በአርአያነት የሚጠቀስ እና በሁለቱ ሀገራት መንግስታት እና መሪዎች ላይ በተደረጉ ለውጦች ተጎድቶ አያውቅም ብሎ ያምናል።

ብልጽግና ፓርቲ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እና ትብብር ሁሌም ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው።

በመሆኑም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች መልካም ጉርብትና፣ ወንድማማችነት፣ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የተሳኩና ውጤታማ እንዲሆኑ የሁለቱ ፓርቲዎች ግንኙነትና ትብብር እንዲጠናከር ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተከበሩ ፕሬዝዳንት

ክቡራን እና ክቡራት

ባለፉት አመታት በጋራ ያስመዘገብናቸው ድሎች ውጤቶች ተባብረን በኛም ሆነ በአለም ላይ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ማሸነፍ ይጠበቅብናል። በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች፣ ሽብርተኝነት እና ሌሎች የደህንነት ስጋቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ሃብት መመናመን፣ የቴክኖሎጂ ስጋቶች እና መርህ የለሽ ጣልቃገብነት ለመግታት ትብብርን ማጠናከር አለብን።

እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ጽናትን የሚጠይቅ ሲሆን አንድ በሚያደርገን መርሆዎች እና እሴቶች ማለትም ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ የህዝብን ጥቅም መደገፍ፣ ወንድማማችነት መተባበር፣ ፈጠራን ማጎልበት እና ሀብታችንን በጋራ መጠቀም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር እንደ ውሃ፣ መብራት፣ የተለያዩ ምርቶች ወዘተ ያሉትን ሃብቶቿን እንደምታጠናክር አረጋግጣለሁ።

የተከበሩ ፕሬዝዳንት

ክቡራን እና ክቡራት

ንግግሬን የምቋጨው በRPP ፓርቲ ህልውና ወቅት ያጋጠሙትን መልካም ነገሮችና ተግዳሮቶች እንወቅ ከዚሁ ጎን ለጎንም ያሉትን እድሎች በመጠቀምና ብሩህ ተስፋን ለመፍጠር ትኩረት እንስጥ ለማለት እወዳለሁ።

ብልጽግና ፓርቲ ለ RPP እና ለጅቡቲ ህዝቦች እድገት፣ ልማት፣ አንድነት እና ብልጽግና ይመኛል።

ብልጽግና ፓርቲ ከእውነተኛ ድጋፍ ጋር ሁሌም ከጎናችሁ እንደሚቆም፣ ለጋራ አላማችንና ራዕያችንም ከጎናችሁ እንደሚቆም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

RPP ለዘላለም ይኑር!

ጅቡቲ ለዘላለም ትኑር!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

በሁለቱ ሀገራት መካከል አርአያነት ያለው ግንኙነት ለዘላለም ይኑር ከፍም ይበል!!

አመሰግናለሁ!

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም