ቀጥታ፡

ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦  ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የቼክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ገለጹ። 

አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የቼክ ሪፐብሊክና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሕዳር ቼክ ሪፐብሊክን ጎብኝተው ከቼክ አቻቸው ፔትር ፊያላ ጋር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ የቼክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔትር ፊያላ በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው ሁለቱ አገራት በግብርና፣ በቱሪዝምና በባህል ዘርፍ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር መምከራቸውን ነው ያነሱት። 

የአገራቱን ግንኙነት በማዕድን፣ በሃይድሮጂኦሎጂና በባህል ዘርፍ ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች አጋርነቱን ለማጠናከር ሁለቱም ወገኖች ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው አገራቸውም በሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት እንደምትሻ ገልጸዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የፖለቲካ ምክክር በቀጣይ ሚያዚያ ላይ ለማድረግ ሁለቱ አገራት አስፈላጊውን ዝግጅት ከወዲሁ እያደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።    

ቼክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያን የልማት ጥረቶች እየደገፈች ያለች አገር መሆኗን አንስተው አሁን ደግሞ የትብብር አድማሱን በማስፋት በአካባቢ ጥበቃና በዘላቂ ልማት ላይ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።   

ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1993 ነበር። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም