በአማራ ክልል የከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማቃለልና አሰራራቸውን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማቃለልና አሰራራቸውን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው
ባህር ዳር፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በከተሞች የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማቃለልና አሰራራቸውን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የከተሞችን የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልከቶ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን መሀመድ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የከተሞች ዕድገት እንዲፋጠን፣ ከተሞች ተወዳዳሪና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ብቃት ያለው የሰው ኃይል፣ አደረጃጀትና ፋይናንስ በመመደብ የከተሞችን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍና የሚሰጡ አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ባህር ዳርን ጨምሮ ስምንት የክልሉ ከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በተለይም የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች የተገልጋይ እርካታን ማረጋገጥ እንዲችሉ የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት ደረጃዎችን በማውጣት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ስራዎች በደብረ ብርሃን፣ ባህር ዳርና ሌሎች ከተሞች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይ በደብረ ብርሃን ከተማ ማዘጋጃ ቤት 38 ሺህ ፋይሎችን ወደ ዲጅታል የማስገባት ስራ በግማሽ ዓመቱ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ከተሞችም ወደዚህ ስርዓት እየገቡ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በቀሪ ከተሞች ፋይሎችን ወደ ዲጂታል ሲስተም የማስገባት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህም የከተማን መሬት ከህገ ወጥ ወረራ ለመከላከል ወደ ካዳስተር የማስገባት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እንዲሁም ከተሞች ከፕላን ዝግጅት ጀምሮ መሰረታዊ ካርታ እንዲኖራቸው በዚህ ዓመት እየተከናወነ ያለው ስራ በመልካም ጅምር የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም በክልሉ 54 ሺህ በመንግስት የሚተዳደሩ ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥም ለቁጥጥር እንዲመች 30 ሺህ ያህሉ ወደ ዲጅታል ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት።
በከተሞች የሚስተዋለውን የቤት ችግር ለማቃለል በግል፣ በማህበራት፣ በሪል ስቴት፣ በመንግስትና ሌሎች የቤት ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለዚህም በግማሽ ዓመቱ 13 ሺህ ቤቶችን በተለያዩ አማራጮች ለመገንባት ታቅዶ እስካሁን በተደረገ ጥረት 4 ሺህ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።