ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራንን የምርምር ተሳትፎና አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የማትጊያ ስርዓት ተግባራዊ አድርጓል

ጎንደር  ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦  የሴት መምህራንን የምርምር ተሳትፎና አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የማትጊያ ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ 

‘’ሳይንስና ሴቶች’’ በሚል መሪ ሃሳብ ሴት መምህራን የምርምር ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት አውደ ጥናት በዩኒቨርሲቲው ዛሬ ተካሄዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራንን የምርምር አቅም በማጎልበት ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያበረክቱ እየደገፈ ነው፡፡

በያዝነው ዓመት ዩኒቨርሲቲው ለ100 ሴት መምህራን በምርምር ዘርፍ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ለሴት መምህራኑ በምርምር ፕሮጀክት አዘገጃጀትና በምርምር ርዕስ አመራረጥ ዙሪያ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ምርምር ስራዎች እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

በሀገር ውስጥና በውጪ ሃገር ጭምር ሴት መምህራን ነጻ የትምህርት እድሎችን እንዲያገኙ ከማመቻቸት ጀምሮ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ጫናዎችን በመቀነስ ለምርምር ስራ ትኩረት እንዲያደርጉ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከ400 በላይ በምርምር ስራዎች ላይ የሚሳተፉ መምህራን እንዳሉት ጠቅሰው፤ ሴት መምህራን በየዓመቱ በሚመደብ በጀት ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሃንስ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ስራዎች ላይ የሴት መምህራን ተሳትፎና ድርሻ 13 በመቶ ብቻ ነው፡፡

አካዳሚው በምርምሩ ዘርፍ የሴት መምህራንን ተሳትፎና አቅም በማጎልበት ሁለገብ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የምርምር ማእከል አቋቁሞ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 

በአውደ ጥናቱ ላይ ሴት መምህራኑ 10 የሚሆኑ የምርምር ውጤቶች ማቅረባቸውን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር የዝቤ ካሳ  ናቸው፡፡

ማህበሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት በመስራት ሴት መምህራን በምርምር ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከማሰልጠን ጀምሮ ወደ አመራርነት ቦታዎች እንዲመጡ እገዛና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በምርምር ስራዎች ተሳታፊ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር መሰረት ሞላ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በምርምሩ ዘርፍ የሴት መምህራን ተሳትፎ አናሳ እንደነበር አንስተዋል፡፡

''ዩኒቨርሲቲው ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የምርምር አጀንዳዎችን ከመቅረጽ ጀምሮ ለምርምር ስራው የሚያስፈልገውን በጀት በመመደብ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እንድናበረክት እያገዘን ነው'' ብለዋል፡፡ 

በአውደ ጥናቱ ላይ ሴት መምህራኑ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በግጭት አፈታትና በተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋም ዙሪያ ያከናወኗቸውን የምርምር ስራዎች አቅርበዋል፡፡ 

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምርምር አውደ ጥናት ላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎችና አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም