ቀጥታ፡

በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል

ሶዶ፤ የካቲት 30/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ መሰብሰቡን የክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ እስራኤል ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት ከተለያዩ አካላት ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል። 

በዚህም በግማሽ በጀት ዓመት በተደረገው እንቅስቃሴ ከቦንድ ግዢ እና ከተለያዩ የሀብት ማሰባሰብ ተግባራት ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። 

የክልሉ ህዝብ ግንባታው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያሳየው ድጋፍና ትብብር የላቀ መሆኑን ጠቁመው፤ ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ ከ669 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል። 

በክልሉ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት በማስመልከት ልዩ መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

በዕለቱም በገቢ አሰባሰብ ሂደት በግምባር ቀደምነት ለተሳተፉ አካላት ምስጋናና እውቅና የሚሰጥ ሲሆን ለግንባታው ቀሪ ስራዎች ማጠናቀቂያ የገቢ ማሰባሰቢያ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

በፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የወላይታ ዞን ኃላፊ አቶ ዘርገነ ወይሻ በበኩላቸው ግንባታው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዞኑ ነዋሪዎች በተለያዩ አማራጮች ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።  

የመንግስት ሰራተኛው፣ አርሶ አደሩና ነጋዴውን ጨምሮ ሁሉም በተቀናጀ መንገድ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ግንባታው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከዞኑ ህዝብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ263 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ገቢ መደረጉን አመላክተዋል። 

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ሶስት ዙር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ አብነት ኤሊያስ፣ "ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅ ድጋፌን አላቋርጥም" ብለዋል ። 

አክለውም "ግድባችን የግንባታ ሂደቱ 95 በመቶ መድረሱን በመስማቴ ደስታዬ ወደር የለውም" ሲሉ ተናግረዋል ። 

''የህዳሴ ግድብ ግንባታ ታሪክ አካል በመሆኔ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል'' ያሉት ደግሞ በወላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ነዋሪና በግል ስራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ሺብሬ ግዛው ናቸው። 

በከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአንድ ወር ገቢ የማሰባሰብ ንቅናቄ የ2 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰዋል። 

''ለግድቡ የምናደርገው በገንዘብ ይሁን በሞራል ድጋፍ ያለማንም ቀስቃሽነት እስከፍጻሜው ይቀጥላል'' ሲሉ ወይዘሮ ሺብሬ አስተያየታቸውን አክለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም