ቀጥታ፡

እንግሊዝ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራች ነው - አምባሳደር ዳረን ዌልች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን የእንግሊዝ እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት በኢንቨሰትመንት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ገለጹ። 

አምባሳደር ዳረን ዌልች፤ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ  ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት ታሪካዊ በሚባለው በዚሁ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በመልካምም ሆነ በአስቸጋሪ ወቅቶች ጥሩ ወዳጅነትና ጠንካራ ትብብራቸው መቀጠሉን ተናግረዋል።


    

የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ ግንኙነቱ በበርካታ መስኮች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።  

ይህም አጋርነት አሁን ላይ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም የትብብር አድማሱን በማስፋት ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አገራቸው ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል። 

ይሄንንም እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ እድሎች መኖራቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል። 

''በቀጣይ ኢትዮጵያ ትልቋ የልማት አጋራችን ትሆናለች'' ያሉት አምባሳደሩ እንግሊዝ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምጣኔዋን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ለማቀላጠፍ በተለይም በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራ ምቹነትን የሚያሳድጉ የማሻሻያ ሥራዎችን ለመደገፍ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።

በሌሎች የልማት መስክ በተለይም በጤና፣ ትምህርትና ሰብዓዊ ጉዳዮች አገራቸው ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

እንግሊዝ ከመቶ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ኤምባሲያቸውን ከከፈቱ ጥቂት አገራት ተርታ የምትመደብ ወዳጅ አጋር ናት። 

ኢትዮጵያና እንግሊዝ በንግድ፣ በባህል፣ በትምህርትና በሌሎች የልማት መስኮች ላይ ጠንካራ አጋርነት ያላቸው አገራት ናቸው።  

ሁለቱ አገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ባለፈ የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስከብሩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም በትብብር ይሰራሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም