ቀጥታ፡

መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች በልዩ ጥራትና ፍጥነት እየተገነቡ ነው - ኦቪድ ግሩፕ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2016(ኢዜአ)፦  መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች የመዲናዋን ዕድገትና ውበት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በልዩ ጥራትና ፍጥነት እየተገነቡ  መሆኑን የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ተናገሩ።

የኦቪድ ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው የኦቪድ ሪል ስቴት ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ነገ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።

በመርኃ ግብሩ የአዲስ አበባን ዕድገትና ውበት ታሳቢ ያደረጉ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮጀክቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል።

ፕሮጀክቶቹ ጫካ መኖሪያ ቤት፣ ሐረር ሆራይዘን፣ ኪንግስ ታወርና አፍሪካን ኃይትስ ሲሆኑ በላቀ ጥራት እየተገነቡ የሚገኙና በቀጣይ የሚገነቡ መሆናቸው ተገልጿል።

የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኦቪድ የ3 ዓመት ስትራቴጂክ የቤት ልማት ዕቅድ በማዘጋጀት በጥራትና ፍጥነት በመገንባት ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። 

የኦቪድ ግሩፕ እህት ኩባንያ በሆነው ኦቪድ ሪል ስቴት በመንግሥት የግል አጋርነት ከ64 ሺህ በላይ ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኃሳብ አመንጪነት እየተገነባ በሚገኘው አዲሱ የጫካ ሳተላይት ከተማ ውስጥ ከ1 ሺህ 900 በላይ ዘመናዊ አፓርትመንቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት አፓርትመንቶችም በ9 ሄክታር መሬት ላይ በሰፊ አረንጓዴ መስክ የሚለሙና ከባለ አንድ እስከ ባለ ሶስት መኝታ ቤቶችን የያዙ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአፍሪካን ሃይትስ መሐል ፒያሳ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሁለገብ አገልግሎቶችን የሚሰጠው ፕሮጀክትም  ከባለ አንድ እስከ ባለ አራት መኝታ የያዙ 324 ቤቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመዲናዋ አዋሬ በተሰኘው አካባቢም 1 ሺህ 780 ዘመናዊ ቤቶች ግንባታቸው መጀመሩን ገልጸዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት ዘመናዊ ቤቶች ከአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ ሳይንስ ሙዚየምና እንጦጦ ፓርክን አያይዘው መዲናዋን ውብ ገጽታ የሚያላብሱ ናቸው ብለዋል።  

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በመዲናዋ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የ60 ሺህ ቤቶች ልማት እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።

በግንባታ ሂደት ከሚገኙት 60 ሺህ ቤቶች ውስጥ 18 ሺህ የሚደርሱ ቤቶችን ለመንግሥት የሚተላለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁም 5 ሺህ ቤቶችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በሽያጭ ለማቅረብ ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል።

ኦቪድ ግሩፕ በቤት ልማት መስክ እያከናወነ የሚገኘው የልማት ሥራዎች የመዲናዋን ገጽታ በመቀየር መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ዘመናዊ ቤት ልማት ፕሮጀክቶቹም አዲስ አበባን ልዩ ውበት ከማላበስ ባሻገር ለኢንዱስትሪው ዕድገትና ልህቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አመላክተዋል።

ነገ ከሚካሄደው የኦቪድ ሪል ስቴት ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያና የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለሕዝብ የማቅረብ መርኃ ግብር ጎን ለጎን ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ የቤቶች ሽያጭ እንደሚኖር ተገልጿል።

"አንድ ቀን፣ አንድ ህልም፣ አንድ እድል" በሚል መሪ ኃሳብ በሚካሄደው የቤት ሽያጭ መርሃ ግብር ለቤት ገዥዎች እስከ 40 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግም ታውቋል።

ኦቪድ ግሩፕ በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት በአዲስ አበባ የኬብል ካር (በገመድ ላይ ተንጠልጣይ የህዝብ ትራንስፖርት) ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ የፕሮጀክት ጥናት ማጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም