የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ለማድረስ የታያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ለማድረስ የታያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እያገዘ ነው
ሀዋሳ ፤የካቲት 29/2016 (ኢዜአ)፦ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ለማድረስ የታያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እያገዘ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
"የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አባልነት ለብልጽግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ የፌደራልና የክልል ምክር ቤት ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴዎች በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ እንደገለጹት፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ህጋዊ የድጋፍ ማዕቀፍ ማግኘቱና ተገቢ ትኩረት መሰጠቱ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1ሺህ 22 ወረዳዎች በላይ ተግባራዊ በተደረገው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ከ54 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በእዚህም ለዜጎች የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ለማድረስ የታያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ጤና መድህን የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ዜጎች መካከል 10 ሚሊዮን የሚሆኑት ከፍሎ መታከም ባለመቻላቸው ወጪያቸው በመንግስት የሚሸፈንላቸው ናቸው ።
"የጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸም እንደ የክልሉ ይለያያል" ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ በአዳዲስ አባላት ምዝገባና እድሳት እንዲሁም የሚሰበሰብ ገቢን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በማድረግ በኩል ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችና ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የማህበረሰብ ጤና መድህንን የትኩረት አጀንዳቸው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ ሲስተር ፈቲያ አህመድ በበኩላቸው፣ መንግስት በጤናው ዘርፍ ካደረጋቸው ለውጦች አንዱ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነት ማጠናከር መሆኑን አስታውሰዋል።
ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ አፈጻጸም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በሲዳማ ክልል ባሉ ሁሉም ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተደራሽ መደረጉንና የአባልነት ምጣኔውም መሻሻሉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዮሐንስ ለታሞ ናቸው።
አገልግሎቱ እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን በማሳደግ ለፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸው፣ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ክልሉ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የመድሃኒት እጥረት ችግር እንዲፈታ የክልሉ መንግስት በየዓመቱ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለመድሃኒት ግዥ እንደሚመድብ ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 14 የህዝብ መድሃኒት ቤቶችን በመክፈት የተጠቃሚውን ቅሬታ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ሳርሚሶ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት እያገኙ ካሉ ሕሙማን መካከል 78 ከመቶ የሚሆኑት የጤና መድህን ታካሚዎች ናቸው።
ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የሆስፒታሉን የገንዘብ አቅም በመደገፍ ለዕቅድ አፈጻጻም ስኬታማነት አስተዋጾ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ከማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴዎች በተጨማሪ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።