በሶማሌ ክልል 900 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፀሐይ ኃይል (ሶላር) መብራት ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

358

ጅግጅጋ፤ የካቲት 29/2016 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል 900 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ (ሶላር) መብራት  ግንባታ ፕሮጀክት  ማጠናቀቁን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የተመራ የፊዴራልና የክልሉ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ቡድን ፕሮጀክቱን ጎብኝቷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ዋርዴር ወረዳ ኩርቱኒ ቀበሌ የሚገኘው የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማምረቻ ፕሮጀክት ግንባታና የሶላር ተከላ ስራ ሙሉ በመሉ ተጠናቋል። 

ፕሮጀክቱ 140 ኪሎ ቮልት የማመንጨት አቅም ያለው በመሆኑ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለማምረቻ ተቋማት፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለመንግስታዊ ተቋማት በቂ ኃይል ማቅረብ እንደሚችል ገልጸዋል። 


 

ከመንግሥት በተመደበ 63 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ መሥመር ተዘርግቶለት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቀዋል። 

የኩርቱኒ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አብዲ ኤሪኮ በሰጡት አስተያየት፤ ፕሮጀክቱ የቀበሌያቸው ነዋሪዎችን ከጨለማ እንደሚያወጣቸው ገልጸው ቀሪ ስራዎች በቶሎ ተጠናቀው አገልግሎቱ እንዲጀመሩ ጠይቀዋል ። 

በሚኒስትር ዴኤታው የሚመራው ቡድን ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በሐረሪ፣ በኦሮሚያና በሌሎች  ክልሎች የፀሐይ ኃይልና የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ እንደሚጎበኝም ታውቋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም