የሴቶችን ምጣኔ ኃብታዊ አቅም በማጎልበት የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ምጣኔ ኃብታዊ አቅም በማጎልበት የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራት ይገባል
አዲስ አበባ ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችን ምጣኔ ኃብታዊ አቅም በማጎልበት የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
አለም ዓቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች ኤይት) ምክንያት በማድረግ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሴቶች ጋር ኢዜአ ቆይታ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ኢዜማ ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ሰብሳቢ ቅድስት ግርማ ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መጨመር በኢኮኖሚ ራሳቸውን መቻል ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ሴቶች በሌሎች ዘርፎችም በአመራርና ውሳኔ ሰጭነት በመሳተፍ አገርና ሕዝብን በማገልገል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በኢኮኖሚ ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው መክረዋል።
መንግሥት ከታች ጀምሮ በትምህርት በማብቃት፣ የተሻለ የገቢ ምንጭ ያላቸው፣ ተወዳዳሪ፣ አገርና ሕዝብን የሚያገለግሉ ሴቶች ለማብዛት ጥረቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ በ6ኛው ፓርላማ በገዥው ፓርቲ የሴቶች ተሳትፎ ከ40 በመቶ በላይ መድረሱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ጠቅሰው ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሴቶችን ለማብቃት ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
የሰረገላ ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንያት ገረመው በበኩላቸው ሴቶች በምጣኔ ኃብት ጠንካራ ሲሆኑ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ በአገር ምጣኔ ኃብት እድገትና ልማት ላይ ጉልህ እስተዋጽዖ ያደርጋሉ ብለዋል።
"እኛ ሴቶች እንደምንችል እንወቅ፣ ብቃት እንዳለን እንወቅ፤ የተሰጠንን እድል ከሰዎች ሳንጠብቅ እራሳችን እንጠቀምበት" ሲሉ አጽንዖት አንስተዋል።
በሴቶች ላይ የሚሰራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋም (ዩ ኤን ዉመን) የፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት ጨረር አክሊሉ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ተግዳሮቶች ከሆኑት ውስጥ አንዱ በኢኮኖሚ አለመብቃት እንደሆነ አንስተዋል።
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ በኢኮኖሚ እራስን መቻል የፖለቲካ ተሳትፎ እድልን በማስፋት፣ የመራጭና ተመራጭነት ተሳትፎ ነጻነትን እድል ያሰፋል።
በመሆኑም ሴቶች በትምህርት እራሳቸውን ለማብቃትና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ የገቢ አማራጮችን አስፍቶ ማየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣት የሴቶች በትምህርት መብቃት አንደኛው አመላካች ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ሥራ ፈጣሪነት ላይ በመሰማራት ራሳቸውን በኢኮኖሚ ለማብቃት እየታዩ ያሉ ለውጦች ዘላቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም የሴቶችን እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዘላቂ ለማድረግ በሕግና በመዋቅር እንዳይቀለበሱ ተደርገው መቀመጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።