ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ፖሊሲ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ፖሊሲ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ፖሊሲ መቀረጹን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
8ኛው ሀገር አቀፍ ኢትዮ-ኸልዝ አውደ ርዕይና ጉባኤ "የኢትዮጵያ የጤና ክብካቤና ቀጣይ ሥራ" በሚል መሪ ኃሳብ የሜዲካል ቱሪዝም የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።
ከየካቲት 28 እስከ 30/2016 ዓ.ም የሚቆይ የጤና ኤግዚቢሽንና ጉባኤ ላይም ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጤና ተቋማት፣ ሙያተኞችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ኢሳያስ መሰለ፤ መንግሥት ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሜዲካል ቱሪዝም ልማት ሥራዎችም በመዲናዋ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥራቱን ያለው አስተማማኝ የጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ለዚህም በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ገቢራዊ የሚሆን የሜዲካል ቱሪዝም ልማት ስትራቴጂክ ፖሊሲ መቀረጹንና ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ፖሊሲው በዘርፉ የግል ባለኃብቶችን ለመሳብ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል።
በዘርፉ የግል አልሚዎችም የመንግሥትን የጤና መሰረተ-ልማት በመጠቀም ጭምር እውቀትና ልምዳቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የሚያለሙበት ሰፊ እድል ተመቻችቷል ብለዋል።
የመንግሥትን የጤና መሰረተ ልማት በመጠቀም ተቋርጦ የነበረው የኩላሊት እጥበት ህክምና በግል ድርጅት አማካኝነት በዳግማዊ ሚኒሊክ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በቀጣይም የመንግሥትና የግል ጤና ልማት ሽርክናን በማጠናከር በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጨምሮ በሌሎችም የሜዲካል ቱሪዝም አገልግሎቱን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ በማይሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ምክንያት ወደ ውጭ ሀገር የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።
በቀጣይ ተግባራዊ የሚሆነው የሜዲካል ቱሪዝም ልማት ስትራቴጂክ ፖሊሲም ለህክምና አገልግሎት ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎችን 80 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ፖሊሲው በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ለማስፋት ያስችላል ብለዋል።
በሂደቱም ባለሙያዎችን በማሰልጠንና አዳዲስ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለሜዲካል ቱሪዝም ልማት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በ8ኛው የኢትዮ-ኸልዝ አውደ ርዕይ የኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 በላይ የሚሆኑ ሀገራት ኩባንያዎች የሕክምና ቴክኖሎጂዎቻቸውን በማስጎብኘት ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።