ቀጥታ፡

በሰው የመነገድና ህገወጥ የድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው-ፍትህ ሚኒስቴር

አዳማ፤የካቲት 29/2016 (ኢዜአ)፡-  በሰው መነገድና በህገወጥ ድንበር ማሻገር ወንጀል ላይ የተሰማሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ  ገለጹ፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር ከፌዴራልና ከክልል የፍልሰት ትብብር ጥምረት አባል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከፌዴራል ፖሊስ ስራ አመራሮች ጋር በህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ በላይሁን ይርጋ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በህገ ወጥ የሰው ዝውውርና በሰው የመነገድ ወንጀል ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከአጎራባች ሀገራት ጋር በመሰራት ላይ ነው።

በዚህም በወንጀሉ የተሰማሩ አካላት ላይ ምርመራ ለማድረግ እንዲቻል ከጅቡቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን አመልክተዋል።

እንዲሁም ከኬንያ ጋር ሥራውን ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡

በህገወጥ የሰው ዝውውርና በሰው የመነገድ ወንጀል ላይ የተሰማሩ ህገወጦች የተደራጁና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙበት  በመሆኑ ለህግ አስከባሪውም ሆነ ለህግ አስፈፃሚው አስቸጋሪ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከተፈራረመቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች በተጨማሪ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በሰው መነገድና በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ዓዋጅን በመጠቀም ወንጀለኞቹን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡


 

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮሚሽነር ሙሊሳ አብዲሳ ኮሚሽኑ በህገወጥ የሰው ዝውውር ላይ የተሰማሩ ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ጉዳዩን የሚከታተልበት ማዕከል በማቋቋም ልዩ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወንጀሉ ተሳትፎ ያላቸውን አካላትን እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመከታተል በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ  ኮሚሽነሩ አውስተዋል።

በሰው የመነገድና በህገወጥ ድንበር የማሻገር ወንጀል የሚሰማሩ አካላትን ያለገደብ በሕግ ጥላ ስር ለማዋል ከክልል ጀምሮ በተቋቋሙ ኮሚቴዎች ዜጎች ህጋዊ መንገድን ብቻ ተከትለው ከሀገር እንዲወጡ ለማድረግ በጥምረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም