ህጻናትን ከዘላቂ የአካል ጉዳት ለመታደግ የሚያስችል የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህጻናትን ከዘላቂ የአካል ጉዳት ለመታደግ የሚያስችል የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ ህጻናትን ከዘላቂ የአካል ጉዳት ለመታደግ የሚያስችል የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጎበና ጎዳና ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም 8 ሚሊዬን የሚደርሱ ህጻናት ከአፈጣጠር ችግር ጋር ይወለዳሉ፡፡
ከነዚህ መካከል ደግሞ አብዛኛዎቹ በታዳጊ ሀገራት የሚወለዱ ሲሆን ኢትዮጵያም የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የቅደመ መከላከል ተግባራትን በማስፋፋት የህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በፖሊሲ ማሻሻያ ፣በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና መረጃ አያያዝ ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች የአፈጣጠር ችግርን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስራ ውጤታማ ለውጥ ማስገኘቱን አመልክተዋል፡፡
የግንዛቤ እጥረት ያለባቸው ወላጆች ከችግሩ ጋር የሚወለዱ ህጻናትን ወደ ህክምና ተቋማት ከመውሰድ ይልቅ በመደበቅ ለዘላቂ አካል ጉዳትና ለተጨማሪ የጤና እክሎች እያጋለጧቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንኑ አጉል አመለካከት ለመቅረፍ ተገቢ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሆፕ ዎክስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው አበራ በበኩላቸው በዋነኝነት የእግር መቆልመም ችግሮችን በፍጥነት በመለየት ህክምና ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም ከአካል ተሃድሶ አገልግሎትና ከጤና ሚኒስቴር ጋር እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ 63 የመንግሥት የህክምና ተቋማት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለህክምና ተቋማቱ የሥልጠና፣ የህክምና ግብዓት አቅርቦት እና ሌሎችንም ድጋፎች በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም በርካታ ወላጆች ህጻናትን ወደ ጤና ተቋም በማምጣት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የእግር መቆልመም እንቅስቃሴን በመገደብ ለዘላቂ የአካል ጉዳት ከማጋለጥ ባለፈ ለማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች የሚዳርግ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የሆፕ-ኤስ.ቢ.ኤች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቤዛ በሻ የህፃናት አፈጣጠር ችግርን በተመለከተ የቅድመ መከላከል ስራ ከመስራት ባሻገር ለሆስፒታሎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደዚሁም ከአስር ሆስፒታሎች ጋር በመቀናጀት የህይወት ዘመን እንክብካቤና ድጋፍ በማዕከልና ከማዕከል ውጭ እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህጻናት የአፈጣጠር ችግሮችን ለመቅረፍ በዕቅድ የሚመራ እርግዝናና የጤና ባለሙያ ምክር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በእርግዝና ወቅት የፎሌት እንክብልንና በፎሊክ አሲድ የበለጸጉ እንደ ሰላጣ አቮካዶ ቲማቲም ፣ ሙዝን የመሳሰሉ ምግቦችን መውሰድ ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል፡፡