ቀጥታ፡

"የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች ህይወታቸው ላለፈ ወገኖች  ያሳዩት ሰብዓዊነት ትክክለኛውን የኢትዮጵያዊ ማንነት አሳይቷል" 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦የጊምቢቹ ወረዳ  ነዋሪዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ  ህይወታቸው ላለፈ ወገኖች ያሳዩት ሰብዓዊነት ትክክለኛውን የኢትዮጵያዊ ማንነት ያሳየ ነው ሲሉ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦች ተናግረዋል ። 

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ አደጋው በደረሰበት የምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ የተገነቡ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተመርቀዋል።  

የአካባቢው ነዋሪዎች ፍጹም ኢትዮጵያዊነት በተሞላበት ጨዋነት የስጋ ዝምድና ለሌላቸው ነገር ግን ሰው ለሆኑ ሰዎች ከልባቸው አዝነዋል፣ የሚገባውን የእምነት ስርአት በማድረግ በተከታታይ ዓመታት ነፍሳቸውን ዘክረዋል፡፡

በአደጋው ቤተሰባቸውን ያጡት ዶክተር እሸቱ ሙላቱ በወቅቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት "የዚህ አካባቢ ሰዎች ለተጎጂዎች ያሳዩት ሰብዓዊነት ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊ ማንነት አሳይቷል" ፡፡

አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢትዮጵያዊ ርህራሄ እንዲሁም ሰውነትን በማስቀደም ለማያውቋቸው ሰዎች ከፍተኛ አዘኔታ ማሳየታቸው የሰውነት ጥግ መገለጫ ነው ብለዋል።

በተከሰተው አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡት ግለሰቦች ከቦይንግ ማህበረሰብ ኢንቨስትመንት ባገኙት ገንዘብ የአካባቢው ነዋሪ ላሳየው ወደር የሌለው ሰብዓዊነት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማስገንባት አበርክተዋል፡፡ 

በሞት ባጣናቸው ቤተሰቦቻችን ስም ለእነዚህ ደጋግ ኢትዮጵያውያን መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ለእነሱ ምስጋናችንን አድርሰናል ብለዋል።

በአደጋው የቤተሰባቸውን አካል ያጡት ወይዘሮ ክበቧ ለገሰ በበኩላቸው የወገኖቻችንን ህይወት ለመዘከር በማሰብ ለአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፉን አድርገናል ብለዋል።

በወቅቱ በደረሰው አደጋው ህይወታቸውን ላጡት ወገኖች መታሰቢያ እንዲሆን የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በመሰረተ ልማት ግንባታው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ተሳትፋለች፡፡

በዚሁ ወቅት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ሊቀጳጳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ጊምቢቹ አካባቢ ማህበረሰብ በመተሳሰብ እና በመፈቃቀር አንድነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የቤተክርስቲያኗ የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሞገስ በአካባቢው የተገነቡት ፕሮጀክቶች ከ13 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የልማት ስራዎቹ በጊምቢቹ ወረዳ ቱላፈራ፣ ሀማ፣ ጎሮ-ትግሬ እና ቢሻን-ጢኖ ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው የተጎጂ ቤተሰቦች ለተከናወነላቸው የመሰረተ ልማት ግንባታ ምስጋና በማቅረብ ለሟቾች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

 

 

 

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም