ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በባለሙያና በአመራር ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ እየተጠናከረ መጥቷል - መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውስጥ የሴት አመራሮችና ባለሙያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች ኤይት) በማስመልከት በየዓመቱ ወደ ተለያዩ አገራት በረራ የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህ ዓመትም በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ትላንት ምሽት ወደ ኢንግሊዝ አገር ለንደን አቅንቷል።


 

በዋና አብራሪ ቃልኪዳን ግርማ  በሚመራው በዚህ ጉዞ ረዳት አብራሪ፣ ቴክኒሻንና የበረራ አስተናጋጆች  ሁሉም ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

ለሴት ሉዑካን ቡድኑም ትላንት ምሽት የሽኝት መርኃ-ግብር ተካሄዷል።  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ አየር መንገዱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ ከ50 በላይ ሴት አውሮፕላን አብራሪዎችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል።

ከ150 በላይ ሴት የአውሮፕላን ቴክኒሻኖች እንዲሁም በአየር መንገዱ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሴት አመራሮች በብዛት ማፍራት እንደተቻለም ነው ያብራሩት።  

አየር መንገዱ የአካታችነት መርህ በመከተል ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የሴቶች ተሳትፎ እየተረጋገጠ መምጣቱን ጠቁመዋል። 

በአየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራው በረራ ወደ ተለያዩ ስምንት ከተሞች ማድረጉ ይታወሳል።

በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ከዚህ ቀደም ወደ  ባንኮክ፣ ኪጋሊ፣ ሌጎስ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኖርዌይ፣ ቦነስ አይረስና ዛንዚባር መካሄዱ ይታወሳል።

ለ9ኛ ጊዜ ዘንድሮ በሴቶች ብቻ የሚደረገው የለንደን ጋትዊክ በረራም በዋና አብራሪ ቃልኪዳን ግርማ የሚመራ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም