ቀጥታ፡

በመቅደላ ወረዳ በ21 ሚሊዮን ብር ወጪ  የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

ደሴ ፤ የካቲት 29 ቀን 2016(ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን  በመቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ በ21 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ፡፡

በምረቃው ስነ-ስርዓት ወቅት የመቅደላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱራህማን ይመር እንደገለጹት ፤ በወረዳው የሰፈነውን ሰላም ከመጠበቅ   ባለፈ በበጀት ዓመቱ በማሻ ከተማ በ31 ሚሊዮን ብር የተለያዩ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ከነዚህም ውስጥ  21 ሚሊዮን ብር  በሆነ ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከተመረቁት መካከል 8 ነጥብ 5 ኪሎሜትር አዲስ ጠጠር መንገድ ግንባታና ከፈታ፣ 24 ክፍል ያለው የሥራ እድል መፍጠሪያ ሸድና ሁለት የኤሌክትሪክ ትራንስፈርመር በመትከል የተሰራው የመብራት ዝርጋታ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

መሰረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ህብረተሰቡ በገንዘቡና በጉልበቱ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ህብረተሰቡ ተገቢውን እንክብካቤና ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ከተማና መሰረተ መምሪያ ኃላፊ አቶ መርከቡ ታረቀ በበኩላቸው፤  በዞኑ የህብረተሰቡን  የመሰረተ ልማት  ተጠቃሚነት ለማሳደግ  በጀት ዓመት በ408 ሚሊዮን ብር ግንባታዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በመንግስት፣ በህብረተሰቡና በአለም ባንክ ድጋፍ  እየተካሄዱ ካሉት ግንባታዎች  መካከል የጠጠርና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ የስራ እድል መፍጠሪያ ሸድና አዲስ መንገድ ከፈታ ይገኙበታል ብለዋል፡፡


 

የከማሻ ከተማ ነዋሪ  አቶ አንዳርጌ ታደሰ በሰጡት አስተያየት በከተማው 02 ቀበሌ አዲሱ ሰፈር ቦታ ተመርተው ቤት ከሰሩ 10 ዓመት ቢሆናቸውም መንገድና መብራት ባለመኖሩ ተቸግረው እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡

ዘንድሮ ጠጠር መንገድ ተገንብቶልንና የመብራት ቆጣሪም በየቤታችን በመግባቱና ችግራችን በመቃለሉ ተደስተናል፤ እናመሰግናለንም ብለዋል፡፡

ለልማቱ በገንዘብና በጉልበታቸው በመደገፍ  የድርሻቸውን እንደተወጡ አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሺዋጋ እሸቱ በበኩላቸው፤ በአካባቢያቸው መንገድ ባለመኖሩ በክረምት ለጭቃ፣ በበጋው ደግሞ በአቧራ ብናኝ ነዋሪው ተችግሮ እንደነበረ አወስተዋል፡፡

ችግሩ እንዲፈታላቸው በጠየቁት  መሰረት  ከመንግስት ምላሽ አግኝተው መንገዱ በመሰራቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

አምቡላንስን ጨምሮ ሌሎች ተሸከርካሪዎችም ወደ አቅራቢያችን  መምጣት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በምርቃው ስነ ስርዓት የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደሩ የአመራር አባላትና የህብረተሰቡ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት በ300 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውም ተመልክቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም