የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የመሰረተ ልምት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

በግምገማ መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምጸሀይ ጳውሎስ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተገኝተዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የተጣለውን ግብ ማሳካት የሚያስችል የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

ነገር ግን አሁንም ስፊ ክፍተቶች እንዳሉ በመጥቀስ፣ የተቀመጠውን ግብ ዕውን ለማድረግ የአመራሩን ቁርጠኝነትና ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በኑሮ ውድነትና በሰላም ጉዳዮች የሚስተዋሉ ችግሮችን ማረምና ሕዝብን መካስ የሚያስችሉ ስራዎችን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ነው ያነሱት።

ለዚህም ከተቋማት መሪዎች እስከ ታችኛው መዋቅር ፈጻሚዎች ድረስ ተቋማቸውን በሙሉ አቅም በአርያነት መምራት እና ሀገርን ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የ2016 ግማሽ ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የመሰረተ ልማትና ማህበራዊ ዘርፍ አጻጸምን ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ዕቅድ መያዙን አስታውሰዋል።


 

ባለፉት ስድስት ወራት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያለው አፈጻጸም ዓመታዊ ዕቅዱን ማሳካት እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በሰብል ምርት ረገድ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 480 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ዘንድሮ 496 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በሆልቲካልቸር፣ በእንስሳትና አሳ ልማት እንዲሁም በሌሎች የግብርናው ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸም እንደተገኘ አንስተዋል።

በመስኖ ስንዴ ረገድም በግማሽ ዓመቱ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ነው የገለጹት።

ከግብርናው ባሻገር በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በገቢ አሰባስብ ረገድም በግማሽ ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ስለመገኘቱ አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም