መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት ይጠናከራሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዓለም አቀፋ የሴቶች ቀን በዓለም 113ኛ በኢትዮጵያ ለ48ኛ ጊዜ "ሴቶችን እናብቃ ሰላምና ልማት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ኃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በአድዋ መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።
የዓለም ሴቶች ቀን ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል የመስራት፣ የመናገር፣ የመሰብሰብና ሌሎችን መብቶች መከበር አለበት በሚል ጭቆናን በመቃወም ለውጥ መምጣት አለበት ብለው የተነሱ ቆራጥ ሴቶች ትግል ውጤት የሚዘክር ዕለት መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
የተደረገው ትግል ፍሬ አፍርቶ አሁን ላይ ሴቶች በአደባባይ ወጥተው ኃሳባቸውን መግለጽ ብቻ ሳይሆን ሴቶች እድሉን ካገኙ በአገር እድገትና ልማት ላይ ውጤት ማምጣት እንደሚቻሉ እያሳዩ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር የሚወክሉት ሴቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ ከቁጥር ባለፈ ሴቶች አቅማቸውን በኢትዮጵያ ልማትና መጻኢ እድል የሚኖራቸው ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የማኅበረሰቡ ልማትና እድገት እንዲፋጠን ሴቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት።
ሴቶች የማህበረሰቡ የጀርባ አጥንት የአገር ዋልታዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ በዚህም መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ካከናወናቸው የለውጥ ስራዎች መካከል አንዱ የሴቶችን የአመራር ተሳትፎ ማሳደግ መሆኑን አመልክተዋል።
ሴቶች በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነትና በየደረጃው ባሉ የሥልጣን ተወረዶች በማምጣት ያላቸውን እውቀትና ጉልበት ለአገር እንዲያበረክቱ የሚያስችል ሥራ በሰፊው መከናወኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ሴቶችን በሥልጣንና በኃላፊነት ቦታ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎችን ጨምሮ በሁሉም መስኮች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት ዘርግቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከማክበር ባለፈ ለሴቶች ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላለፉት ወራት ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር አገራዊ እቅድ በማውጣት ውይይቶችና የንቅናቄ ሥራዎች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።
ለ23 ሺህ 932 አቅመ ደካማ ሴቶችና ሕጻናትም ከ99 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ድጋፍ መደረጉንና በአጠቃላይ ሴቶችን በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄም እስከ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ጠቁመዋል።