በአነስተኛ ገንዘብ የጀመርነው የወተት ላም እርባታ ሥራ ተጠቃሚ አድርጎናል - ኢዜአ አማርኛ
በአነስተኛ ገንዘብ የጀመርነው የወተት ላም እርባታ ሥራ ተጠቃሚ አድርጎናል

ማይጨው፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ በአነስተኛ ገንዘብ የጀመርነው የወተት ላም እርባታ ሥራ የዕለት ወጪያችንን ከመሸፈን አልፎ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ በማይጨው በከተማ ግብርና የተሰማሩ ነዋሪዎች ገለጹ።
በከተማዋ በወተት ላም እርባታ ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ያመረቱትን ወተት በመሸጥ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን የገበያ ትስስር ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል ።
በከተማ ግብርና ተሰማርተው በወተት ላም እርባታ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ የሚገኙት ነዋሪዎች እንዳሉት የወተት ምርቱን በመሸጥ የዕለት ወጪያቸውን ከመሸፈን ባለፈ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በወተት ላም እርባታ ተሰማርቶ ውጤታማ ከሆኑት መካከል ወጣት ዳዊት ዮሃንስ አንዱ ነው።
ከአራት አመት በፊት በዘጠኝ ሺህ ብር አንድ የወተት ላም በመግዛት የጀመረው የእርባታ ሥራ አሁን ላይ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልጿል።
በቀን ከአንድ ላም ከአስር እሰከ 15 ሊትር ወተት በማግኘት ለገበያ እንደሚያቀርብ የገለፀው ወጣቱ የገበያ ትስስር ችግር ባይገጥመው ከተጠቀሰው በላይ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አስረድቷል።
በአንድ ላም የጀመሩት ስራ በአሁኑ ወቅት 10 መድረሳቸውን የገለጹት ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ መረሳ በርሀ በቀን ከአንድ ላም እስከ 12 ሊትር ወተት በማግኘት ሸጠው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
''በየቀኑ ከዚህ በላይ ወተት ማቅረብ ቢቻልም የገበያ ትስስር አለመኖሩ ግን በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል'' ብለዋል።
በወተት ላም እርባታ የተሰማሩት ሌላኛው አቶ ሐጎስ ባራኪ በበኩላቸው፣ከሚያረቧቸው የወተት ላሞች በየቀኑ እስከ 12 ሊትር ወተት በመሸጥ ቋሚ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የእንስሳት ቀለብ እጥረት በማጋጠሙ በቀን ከአንድ ላም ይገኝ የነበረው የወተት መጠን ሊቀንስ መቻሉን ተናግረው እንደዛም ሆኖ የገበያ ትስስር ቢፈጠር የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የማይጨው ከተማ የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ፅህፈት ቤት ተወካይ ዶክተር ፀጋይ ተካ እንደገለፁት፣ በከተማዋ ከሁለት ሺህ 900 በላይ የወተት ላሞች አሉ።
መንግስት አርሶ አደሮቹን በማደራጀት ሼድ ከመስጠት አንስቶ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን የገለፁት ተወካዩ ከራያ ቢራ ፋብሪካ ጋር በመነጋገር አርሶ አደሮቹ ተረፈ ምርቱን ወስደው ለመኖ አገልግሎት እንዲጠቀሙ ማድረጉን ተናግረዋል።
አምራቾች ያመረቱትን ወተት ለቤት ፍጆታ ከተጠቀሙ በኋላ ወደ ገበያ ይዘው ስለሚወጡም የገበያ ችግር እንደሚያጋጥማቸው አስረድተዋል።
ስለሆነም ፅህፈት ቤቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በማሰብ አርሶአደሮች በማህበር ተደራጅተው ማቀዝቀዣ ማሽን ገዝተው ወደ መቀሌና ሌሎች አካባቢዎች የሚልኩበትን መንገድ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በማይጨው ከተማ በከተማ ግብርና ከተሰማሩ ነዋሪዎች መካከል ከ340 በላይ የሚሆኑት በወተት ላም እርባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንደሆኑም ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።