ቀጥታ፡

ለዘንድሮ የበልግ ወቅት የግብርና ሥራ እስካሁን ከ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦  በዘንድሮ የበልግ ወቅት የግብርና ሥራ ለማረስ ከታቀደው 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መታረሱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።  

በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኑኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ከበደ ላቀው ለኢዜአ እንዳሉት የመኸር ወቅት ሥራዎች በስኬት ተጠናቆ የበጋ መስኖ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። 

በዚህም የበጋ መስኖ ሥራዎች መልካም አፈጻጸም እየተገኘበት መሆኑን ጠቁመው አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ሥራ እየተሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዘንድሮ የበልግ ወቅት ከጥር ጀምሮ ከባለሙያው እስከ አርሶአደሩ ድረስ ግንዛቤ ተወስዶ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ በሰጠው መረጃ መሰረት የዝናቡ ሥርጭት በበልግ ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል። 

በልግ አብቃይ በሆኑ ዝናብ በሚደርስባቸው አካባቢዎች ወደ ተግባር ሥራ መገባቱን ገልጸው ዝናቡን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዘንድሮ የበልግ ወቅት ለማረስ ከታቀደው 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መታረሱን ጠቁመዋል። 

ከዚህም 200 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በዘር መሸፈኑንም ገልጸዋል።

የዚህን የበልግ ወቅት ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የግብዓት አቅርቦት ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በግብርና ሜካናይዜሽን ከኮሪያ የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር የትራክተር አጠቃቀም እንዲሁም ጥገና ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም የ 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ገልጸው ይህንንም የማጓጓዝ ሥራ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የእርሻ ሥራ ለማከናወን ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጹ ይታወሳል። 

አብዛኛው የበልግ አብቃይ አከባቢዎች በመጠንም ሆነ በስርጭት ከዕለት ወደ እለት የተስፋፋና የተጠናከረ እርጥበት ስለሚኖራቸው የእርሻ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም እንዲሁ። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም