13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ በጋና ይጀመራል።
ውድድሩን ያዘጋጁት የአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበርና ከአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር ጋር በመተባበር ነው።
በውድድሩ ላይ ከ4000 በላይ አትሌቶች በ29 የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከስፖርት አይነቶቹ ስምንቱ በፓሪስ በሚደረገው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማለፍ የሚያስችሉ ውድድሮች ናቸው።
ኢትዮጵያም በውድድሩ በዘጠኝ ስፖርቶች 149 ስፖርተኞች የምታሳትፍ ሲሆን ከነዚህም አምስቱ የኦሊምፒክ ውድድሮችና አራቱ የኦሊምፒክ ውድድር ያልሆኑ ስፖርቶች ናቸው።
አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌትና ወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የውድድር አይነቶች ናቸው።
ዝላይና ዲስከስ ውርወራ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከምትሳተፍባቸው የውድድር አይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተለያዩ ዙሮች ተከፋፍሎ ጋና መግባቱን ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አክራ በሚገኘው የጋና ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ስታዲየም ይከናወናል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማና ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች እንደሚገኙ ከአፍሪካ ሕብረት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ውድድሩ በአክራ፣ ኩማሲና ኬፕ ኮስት ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።
ውድድሩ እ.አ.አ በ2023 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በውድድሩ አዘጋጆች መካከል በነበረ የገበያ መብቶች አለመግባባት ወደ 2024 መዘዋወሩ የሚታወስ ነው።
የአፍሪካ ጨዋታዎች (በቀድሞ ስያሜው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች) በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ውድድር ነው።
የአህጉራዊው ስፖርት ውድድር ኃሳብ የተጠነሰሰው እ.አ.አ በ1963 በሴኔጋል በተካሄደ የስፖርት ፌስቲቫል ነው።
በዛው ዓመት የአፍሪካ የወጣትና ስፖርት ሚኒስትሮች ሴኔጋል ላይ ባደረጉት ስብስባ ውድድሩ የመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች ተብሎ እንዲካሄድ ከውሳኔ ላይ ደረሱ።
የመጀመሪያው ውድድር እ.አ.አ በ1965 በኮንጎ ብራዛቪል የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ላይ ከ30 አገራት የተወጣጡ ከ2500 በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።