ኢትዮ ቴሌኮም በዲጂታል አካታችነት ሴቶችን ማብቃት የሚያስችል ስምምነት “ኮኔክትድ ውሜን” ከተባለ ኢኒሼቲቭ ጋር ተፈራረመ

190

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም በዲጂታል አካታችነት ሴቶችን ማብቃት የሚያስችል ስምምነት “ኮኔክትድ ውሜን” ከተባለ ኢኒሼቲቭ ጋር ተፈራርሟል።

ስምምነቱ የዲጂታል ስርዓተ-ፆታ ልዩነትን ለማጥበብ እና የሴቶችን የዲጂታል ተካታችነት ማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

ስምምነቱን የኢቲዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከኢኒሼቲቩ የስራ ሃላፊዎች ጋር በስፔን ባርሴሎና መፈረማቸውን ከኢቲዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ስምምነቱ የሴቶችን የሞባይል ኢንተርኔት እና የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት/ቴሌብር/ ተጠቃሚ ቁጥር እ.ኤ.አ እስከ 2026 በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ያለመ ሲሆን አካታች የሞባይል ኢንተርኔት እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ማቅረብን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት ኩባንያው አሁን የሚታየውን የዲጂታል ስርዓተ-ፆታ ክፍተት ለማጥበብ የሞባይል ኢንተርኔትና የሞባይል ፋይናንሺያል አገልግሎቶችን ለሴቶች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ሴቶች በዲጂታል ኢኮኖሚው ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም