ቀጥታ፡

ዲያስፖራው በክልሉ ልማት በስፋት መሳተፍ እንዲችል ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው- የኦሮሚያ ክልል

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦  በኦሮሚያ ክልል ዲያስፖራው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ዲያስፖራ የኢንቨስትመንት ተሳትፎና የማህበረሰብ ልማት የጋራ ምክክር መድረክ በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተካሄዷል።


 

የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልዓዚዝ ዳውድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ ዲያስፖራ በኢንቨስትመንትና በልማት መሳተፍ እንዲችል ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የክልሉ ዲያስፖራ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በርካታ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁንም ዲያስፖራው የሚያደርገው ተሳትፎ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግስት የዲያስፖራውን የልማትና የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ዲያስፖራ ተሳትፎ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አሚን ጁንዲ፣ የክልሉ ዲያስፖራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ከክልሉ አልፎ በአገር ደረጃ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ያሉ ዲያስፖራዎች በርካታ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይም የክልሉ ዲያስፖራ በአገር ልማትና እድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል አስፈላጊ ድጋፎች እንደሚደረጉም ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዲስትሪ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ ደነቀው በበኩላቸው ቢሮው ለዲያስፖራው ምቹ የሆኑ አሰራሮች እየዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲያስፖራ አባላትም ከአገልግሎት ዘርፍ ይልቅ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሰማራት ለዜጎች ስራ መፍጠር የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ መክረዋል።

ቢሮው በሚችለው አቅም ሁሉ ለዲያስፖራው የልማት ተሳትፎ ማነቆ ሆነው የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ዲያስፖራው በሚችለው አቅም አገሩን እንዲያግዝ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይ አቅናው ናቸው።

አገልግሎቱ ከተለያዩ አገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን ቀምሮ የዲያስፖራውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ የዲያስፖራ አባላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም