በቢሾፍቱ አካባቢ ደርሶ በነበረው የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ መታሰቢያነት የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ሥራ ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በቢሾፍቱ አካባቢ ደርሶ በነበረው የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ መታሰቢያነት የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ሥራ ጀመሩ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦ ከአምስት ዓመታት በፊት ቢሾፍቱ አካባቢ ደርሶ በነበረው የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ መታሰቢያ የሚሆኑ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ኬንያ በበረራ ላይ እንዳለ ባጋጠመው ችግር መከስከሱ ይታወሳል።
የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ሰዎችን አሳፍሮ በጉዞ ላይ የነበረው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከ6 ደቂቃ በኋላ ቢሾፍቱ አካባቢ ልዩ ስሙ ቱሉ ፈራ በተባለ ሥፍራ ተከስክሷል።
በዚህ አደጋ የ157 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን የአደጋው መነሻም የአውሮፕላን አምራቹ የቦይንግ ችግር መሆኑ ተረጋግጧል።
በመሆኑም ከአምስት ዓመታት በፊት የደረሰውን አደጋ ምክንያት በማድረግ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማኅበራዊና ልማት ኮሚሽን በ125 ሚሊየን ብር የተለያዩ መሠረተ- ልማቶችን አደጋው በደረሰበት አካባቢ ገንብተው ለአካባቢው ማኅበረሰብ አስረክበዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማኅበራዊና ልማት ኮሚሽን ዳይሬክተር በቀለ ሞገስ፤ ከተገነቡት ፕሮጀክቶች መካከል ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያ፣ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እና ሌሎችም የሚገኙበት መሆኑን ገልፀዋል።
የገንዘብ ድጋፉም በቦይንግ ማኅበረሰብ ኢንቨስትመንት ፈንድ 100 ሚሊየን ብር እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማኅበራዊና ልማት ኮሚሽን የ25 ሚሊየን ብር ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል።
አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ ከ13 ሺህ 800 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአውሮፕላን አደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎችም መታሰቢያ የሚሆን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በሥፍራው በመገኘት ፕሮጀክቶቹን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትሮች አካባቢ ርቀት ላይ ከምትገኘው ቱሉ ፈራ ሜዳ ላይ የወደቀውን የአውሮፕላኑን ስብርባሪና የአደጋውን ሰለባዎች አካል ለማግኘት የቀናት ቁፋሮ አስፈልጎ ነበር።
የአካባቢው ማኅበረሰብም በወቅቱ በደረሰው አደጋ በእጅጉ በመደናገጥና በሥፍራው በመገኘትም ሀዘናቸውን በተለያዩ መንገዶች መግለፃቸው ይታወሳል።