ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጀርመን በሰላምና ልማት እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች ይበልጥ ተቀራርበው ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያና ጀርመን በሰላምና ልማት እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች ይበልጥ ተቀራርበው የሚሰሩ መሆኑን ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የጀርመን የፓርላማ አባላት ልዑካን ጋር ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ዋነኛ ጉዳይም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ፤ ኢትዮጵያና ጀርመን የቆየ ታሪካዊ፣ የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር ያላቸው አገራት መሆኑን አንስተዋል።


 

በውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር መስኮች፣ በሰላምና በጂኦ-ፖለቲካል ዘርፎች ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የማዕድን፣ የማኑፋክቸሪንግና ሌሎችም የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢሳተፉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን አጠቃላይ የልማትና የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ እንዲሁም የባህር በር ለማግኘት እያከናወነች ያለውን ጥረት በተመለከተም ዶክተር ዲማ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው ስምምነትም ይህንን ጥያቄ በመመለስ፣ በጋራ በመልማት፣ የአካባቢ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ጨምሮ መንግሥት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እንዲሁም ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በሶማሊያ፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሚና ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።

የተፈጥሮ ኃብትን በጋራ መጠቀምንና በኃይል ልማት ትስስር ለመፍጠር የተገነባው የሕዳሴ ግድብም ግንባታው በመገባደድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በየዓመቱ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ልማትም ከሀገር አልፎ አህጉራዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገና፤ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በጀርመን ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ስቴፋን ኪዩተር፤ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል።


 

የጀርመን ፓርላማ አባልና የአፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ቃል-አቀባይ እና የምጣኔ ኃብትና ልማት ትብብር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲፕል ዲሚተር ፍሪዶፍ፤ በዓለም እንዲሁም በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በዚህ ረገድ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ ተቀራርባ የምትሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የጀርመንና የኢትዮጵያ ፓርላማ ተወካዮች የሁለቱን አገራት በምጣኔ ኃብት፣ በፖለቲካ፣ በፓርላማ ግንኙነት፣ በሰላምና በሌሎችም የትብብር መስኮች ላይ በጋራ የሚሰሩ መሆኑን በውይይታቸው አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም