ቀጥታ፡

በመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ ከ900 ለሚልቁ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከ900 ለሚልቁ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ሥልጠና መስጠቱን ገለጸ፡፡ 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በምክር ቤቱ የሁለት ዓመታት ሪፖርት፣ የግልግል ዳኝነትና የኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡


 

የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ፤ ምክር ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአዲስ አበባ እና ከክልል ከተሞች ለተውጣጡ 393 የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠቱን ገልፀዋል። 

ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ በድምሩ ለ933 የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል ብለዋል።

የሥልጠናው ይዘቶች በጥላቻ ንግግር፣ በሰላም ጋዜጠኝነትና በግጭት አገናዛቢ ዘገባ እንዲሁም ሌሎች ርዕሰ- ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ዘርዝረዋል። 

በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሕጋዊ መንገድን ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመው፤ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንም የበኩሉን በመወጣት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ምክር ቤቱ ዕቅዶቹን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የበጀትና የፀጥታ ችግሮች ፈተና እንደሆኑበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልፀዋል።  

በየጊዜው እየናረ የሚገኘው የሕትመትና ሳተላይት ዋጋ መጨመር መገናኛ ብዙኃን ላይ አደጋ መደቀኑን ጠቁመው፤ በመንግሥት ድጋፍና እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ፤ የምክር ቤቱ መጠናከር ለመገናኛ ብዙኃን ዕድገት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለምክር ቤቱ መጠናከር የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል። 

በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ የ2016 እና 2017 ዓመታዊ ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ በተጓደሉ የምክር ቤቱ አመራርም ምትክ ምርጫ ተከናውኗል።

በ2011 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት 82 የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አባላት እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም