ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን ቀደምት ጀግኖች ለፈፀሙት አኩሪ ድል ቋሚ ቅርስ ነው

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፡- የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን ቀደምት ጀግኖች ለፈፀሙት አኩሪ ድል ቋሚ ቅርስ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች ገለጹ።

የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች የአድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።


 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ፤ የአድዋ ድል የመላ ኢትዮጵያውያን ኩራትና የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ይህንን ታላቅ የድል ታሪክ የሚመጥንና በቋሚነት የሚዘክር መታሰቢያ መገንባቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የድል መታሰቢያው ቀደምት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለፈፀሙት አኩሪ ድል ቋሚ ቅርስ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአድዋን ታሪክ በቅጡ እንድናውቅ ያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም የአድዋን ጀግኖች ታሪክ በቅጡ አውቆ እንዲዘክረው መታሰቢያው ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።


 

የአድዋን ድል በመሰነቅ ትውልዱ ለሀገሩ እድገትና ብልፅግና መሥራት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መታሰቢያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሌሎች የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም የድሉን መታሰቢያ በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ መመረቁ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም