የወልደሀኔ- ዱርጊ የ41 ኪሎሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወልደሀኔ- ዱርጊ የ41 ኪሎሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሊካሄድ ነው
ታርጫ ፤ የካቲት 28 /2016 (ኢዜአ) ፡- የወልደሀኔ- ዱርጊ የ41 ኪሎሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ ።
የመሰረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድ አብዱረሐማን ናቸው።
የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ የዳውሮ ዞንን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጣምባሮ ልዩ ወረዳን ጨምሮ ሌሎችንም የሚያገናኝ ነው፤ ይህም ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድ አብዱረሐማን በወቅቱ እንዳሉት ፤የመንገዱ ግንባታ የረጅም ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄን የሚመልስ ነው።
አካባቢዎቹ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንዲሁም ሌሎች በከፍተኛ መጠን የሚመረትባቸው እንደሆኑ እንደሚያውቁ አውስተው ፤የመንገዱ መገንባት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትም የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የመሰረተ ድንጋይ ዛሬ የተቀመጠለት የወልደሀኔ- ዱርጊ የ41 ኪሎ ሜትር በላይ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 2 ቢሊዮን 873 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ እንደሚገነባ አስታውቀዋል።
የግንባታው ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን እንደሆነም ኢንጅነር መሐመድ ገልጸው፤ ግንባታው በሶስት ዓመት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አመላክተዋል ።
ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት የመንገድ ፕሮጀክት ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሁሉም አካላት ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋልም ብለዋል።
በክልሉ የተጀመሩ የተለያዩ የመንገድ ግንባታዎችም ያለባቸውን ችግር በመፍታት በጥራት እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እንደሚደረግም ኢንጅነር መሐመድ ጠቁመዋል።
የወልደሀኔ-ዱርጊ የመንገድ ግንባታ የአካባቢው ህብረተሰብ ለዘመናት ሲያነሳው የቆየው ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑ እንኳን ደስአላችሁ ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው የመንገድ ግንባታ ጥያቄ በተለያየ ምክንያት ሲንከባለል ቆይቶ ዛሬ ላይ ምላሽ ማግኘቱ መንግስት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
መንገዱ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የአመራር አባላትና የአካባቢ ነዎሪዎች ተገኝተዋል።