ኦቪድ ግሩፕ የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት የሚያስችል የኬብል ካር ቴክኖሎጂ ተግባራዊ  ሊያደርግ ነው

305

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦ ኦቪድ ግሩፕ የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት የሚያስችል የኬብል ካር (በገመድ ላይ ተንጠልጣይ የህዝብ ትራንስፖርት) ቴክኖሎጂ ተግባራዊ  ሊያደርግ  መሆኑን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ታደሰ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነትና ለልማቱ ባላቸው ቁርጠኝነት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች ሀገሪቷን በብዙ መልኩ ወደ ፊት የሚያራምዱ ናቸው ብለዋል።

በሀገራዊ ልማትና በተለይም በግንባታው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ ከኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርጓል። 

ስራ አስፈጻሚው በማብራሪያቸው፣ ኦቪድ ግሩፕ በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት በአዲስ አበባ የኬብል ካር ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያጎሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን  ተናግረው፣ ኦቪድ ግሩፕም በግንባታው ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት በመንግስት የሚደረገውን ጥረት የበለጠ የሚደግፍ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኦቪድ ግሩፕ በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት በአዲስ አበባ የኬብል ካር ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ የፕሮጀክት ጥናት ማጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል።

የባቡር እና የመኪና መሰረተ ልማቶችን ማፍረስ ሳያስፈልግ በገመድ ላይ ተንጠልጣይ የህዝብ ትራንስፖርት ወይም ኬብል ካር ቴክኖሎጂን በአዲስ አበባ ተግባራዊ ለማድረግ ያሰችላል ብለዋል።


 

መንግስት አቅመ ደካማና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ኑሮ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ለስኬታማነቱ ኦቪድ እገዛና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከማሳመር ባለፈ የነዋሪዎችን ሕይወት የሚቀይሩና ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ኦቪድ በዚህ ረገድ ከመንግስት ጋር በመተባበር የራሱን አሻራ እያሳረፈ ይገኛል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር የአዋሬ መንደር ልማት እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አመራር፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ እናቶች የስራ ዕድል የፈጠረ የእንጀራ መጋገሪያ ማዕከል በመገንባት ኦቪድ መሳተፉን አንስተው ከግንባታ ባሻገር ማህበራዊ ሃላፊነቱን በተጠናከረ መልኩ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በሁሉም የልማት መስኮች የመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት እየተጠናከረ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ዮናስ፤ በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብና ቁርጠኝነት ሀገሪቷን ወደ ፊት የሚያራምድ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ዕምቅ ጸጋዎችን በማልማት ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለትውለድ ተግባራዊ ያደረጓቸው ፕሮጀክቶች ሁነኛ ማሳያ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የኦቪድ የቤት ግንባታ አካሄድ በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያለውን ብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በአጭር ጊዜና በጥራት በመገንባት ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመኖሪያ ቤት ግንባታ ስራ አሁን እየተጠቀመ ካለው ቴክኖሎጂ ባለፈ በቅርቡ ሌላ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ኦቪድ ሀገራዊ ልማትን ከማገዝ ባለፈ በግንባታው ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀምና በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ስራውን ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም