ኢትዮጵያ በኢነርጂና አቪዬሽን ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በኢነርጂና አቪዬሽን ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኢነርጂና አቪዬሽን ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም(ዶ/ር) በወቅታዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ (ዶ/ር) በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው በኢነርጂ እና አቪዬሽን ዲፕሎማሲ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር እየሠራች መሆኑን አንስተዋል።
ቃል አቀባዩ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኬንያ እና በታንዛኒያ ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝትና የተፈረሙ ሥምምነቶች መካከል የኢነርጂ እና አቪዬሽን ዘርፎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ይህም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መሥጠቱን ያመለክታል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የኢትዮጵያ በቀጣናዊ ትስስር እና ትብብር ላይ ያላት ተፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ማብራራታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ አጋር መሆኗ የታየበት እንደሆነም ነው አምባሳደር መለስ(ዶ/ር) የገለጹት።
ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታከናውነው የኃይል ሽያጭ የደቡባዊና ምዕራብ አፍሪካ የሚሻግር የኢነርጂ ትስስር የአህጉሩ ፕሮጀክት አካል ይሆናል ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለዳሬሰላም አራት መቶ ኪሎ ቮልት በሽያጭ መልክ ለማቅረብ መስማማቷ ኢነርጂ የዲፕሎማሲ አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል።
በአቪዬሽን የዲፕሎማሲ መስክ በበረራ ያለውን ትብብር ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ስምምነቱ ያግዛል ሲሉም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2023 ድረስ 75 የታንዛኒያ አብራሪዎች እና 25 በዘርፉ የሚሰሩ የበረራ ቴክኒሺያን በኢትዮጵያ ሥልጠና ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
ሌሎች በሳምንቱ በሚኒስትር ዴኤታዎች የተከናወኑ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም በመግለጫቸው ማብራራታቸውም ተመላክቷል።