በኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑክ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑክ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑክ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤው “ደህንነቱ ለተጠበቀ ነገ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል ትብብር” በሚል መሪ ቃል እ.ኤ.አ ከማርች 5 እስከ 7/2024 በዱባይ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራው ልዑክ ቡድን እየተሳተፈ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ የዱባይ ፖሊስ ዋና አዛዥ ሌተና ጀነራል አብዱላህ ከሊፋ አል ማሪ ጋር በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተጠናከረ ግንኙነት እንዳላት የገለፁት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ይህንን ግንኙነት በፖሊስ ዘርፍም የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ አመራሮች በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ ልውውጥ፣ በቪ.አይ.ፒ ጥበቃ፣ በአቪዬሽን ደኅንነት፣ በፈንጂ ቁጥጥርና በሁነት ደኅንነት እንዲሁም በሎጀስቲክ ድጋፍ ለማድረግ እና አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በዱባይ ኢንተርኔት ሲቲ ሞቶሮላ ማዕከል ቴክኒካዊ ስልጠና እየወሰዱ ያሉትን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ሙያተኖችን መጎብኘታቸውና የስልጠና ሂደቱን መከታተላቸው ተጠቁሟል።
ስልጠናውን እየሰጡ ካሉ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሞቶሮላ ሶሉሺን ዳይሬክተር ዩቫል ሀናን እና ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት የሞቶሮላ ሲስተም ኢንጂነር ሙሉጌታ መለሰ ጋርም ውይይት አድርገዋል፡፡
ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ የህግ አስከባሪ አካላትን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና የወንጀል ስጋቶች እየጨመሩ ባሉበት በዚህ የዲጂታል ዘመን ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤው ከ138 ሀገራት የተውጣጡ የፖሊስ አመራሮችን ያገናኘ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
ደህንነቱ ለተጠበቀ ነገ፣ ለብሩህና ለተሻለ ህይወት ጠንካራ ግንኙነትን የሚገነቡበት መሆኑም በመረጃው ተጠቅሷል።
በሽብርተኝነት፣ በተደራጁ ወንጀሎች፣ በኢኮኖሚ ወንጀሎች፣ በህገ-ወጥ የገንዘብና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ በሳይበር ወንጀል፣ በፎረንሲክ ሳይንስ፣ በትራፊክ ደህንነት እና በሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት አንገብጋቢ ጉዳዮች እና ተግዳሮቶች ላይ የተዘጋጁ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት መደረጉም ተገልጿል፡፡
የፖሊስ ሥራዎችን ለማጠናከርና ለማኅበረሰብ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ድሮኖች ያላቸው አስተዋፅኦ ላይ የጉባኤው ተሳታፊዎች ውይይት ያካሄዱ ሲሆን ወንጀልን በመቀነስ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ተግባራዊ ሊደረጉ በሚገቡ ዘዴዎች ላይም መክረዋል፡፡
የዲ ኤን ኤ ላቦራቶሪ ለፎረንሲክ ምርመራዎች ያለው አስተዋፅኦ፣ የተባበሩት መንግስታት የሕገ-ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እና የሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮችን የመከላከል ስትራቴጂ፣ ዓለም አቀፍ ትብብር የዕፅ ዝውውሩን በመቀነስ ረገድ ያለው ሚና፣ ወጣቶችን ከአደንዛዥ እፅ ሱስ ለመከላከል የተቋማት፣ የኅብረተሰብ እና የስነ-አእምሮ ህክምና ሚና፣ አደንዛዥ ዕፅን ለመዋጋት የሚያግዙ ምርጥ ልምዶች እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ተሳታፊዎች መጋራታቸው ተመላክቷል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጣይ የወንጀል ተግዳሮቶችን ለመዋጋት ጉባኤው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውም በመድረኩ መገለጹም ተገልጿል፡፡