ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክን ከመሰነድ ባሻገር ትውልዱ ከድሉን እሴቶች እንዲማር ያስችላል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፡- የአድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክን ሰንዶ ለቀጣዩ ትውልድ ከማሻገር ባለፈ ትውልዱ ከድሉ እሴቶች በመማር የራሱን ታሪክ እንዲሰራ ዕድል እንደሚሰጥ ተጠቆመ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመራሮች፣ የክልልና ከተማ መስተዳድር ኢንቨስትመንት ኮሚሽነሮች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርክ ተወካዮች የአድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል። 

የጉብኝቱ ታዳሚዎች ለመላው የጥቁር ሕዝቦች ትግል ፋና ወጊ የሆነው የአድዋ  ትሩፋቶችና ቅርሶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳገቶ ኩምቢ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በአድዋ የቀደሙ አባቶች በኅብረት በመነሳት ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለሌሎች  ጥቁር ሕዝቦች አኩሪ ታሪክ ጽፈዋል።     

በአድዋ ድል የተሳተፉ አባቶች በጽናትና በጀግንነት ተዋግተው ድል አድርገዋል ያሉት ምክትል  ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያን ለመለወጥ ብዙ ትምህርት የሚገኝበት ነው ብለዋል።

በአድዋ ድል መስዋዕት ሆነው ያለፉ አባቶች ነፃ አገርን አስረክበውናል፤ አሁን ደግሞ በልማት፣ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ትውልዱ የራሱን ድል ማስመዝገብ ኃላፊነት ተጥሎበታል ሲሉ ተናግረዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋን ድል መዘከር የሚያስችል ቅርስ መሆኑን ጠቁመው፤ ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክን ከመሰነድ ባሻገር ኢትዮጵያን ወደ ሌላ ከፍታ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል።    

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለቱሪስት ፍሰትን የመጨመርና የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው።


 

በኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የዕቅድ ክፍል ዳይሬክተር አብዱራሂም ሐሰን በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋን ታሪክ የሚመጥን ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።   


 

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ ሐሰን፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀጣዩ ትውልድ በተነቃቃ መንፈስ እንዲሰራ፤ ባህልና ትሩፋቱን በአግባቡ እንዲገነዘብ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

 

 

 

 

 

    

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም