የፓርኮች ልማትን በማጠናከር ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - አቶ ኩመራ ዋቅጅራ - ኢዜአ አማርኛ
የፓርኮች ልማትን በማጠናከር ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - አቶ ኩመራ ዋቅጅራ
ጋምቤላ ፤የካቲት 27/2016 (ኢዜአ)፡- የብሔራዊ ፓርኮችን ልማትን በማጠናከር ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ አስታወቁ።
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኩመራ ዋቅጅራ፣ ኢትዮጵያ ካሏት አጠቃላይ የመሬት ስፍት 10 ነጥብ 6 ከመቶ የሚሆነው እምቅ የብዝሃ ህይወት ሀብት ያላቸው ብሄራዊ ፓርኮች፣ የእንስሳት መጠለያና ጥብቅ ስፍራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያም እየተገበረች በምትገኘው የ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ውስጥ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መስጠቷን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሀብት ቢኖራትም ከቱሪዝም ሀብት ተጠቃሚ ሆናለች ብሎ ለመናገር አያስደፍርም ብለዋል።
ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል ለሀብቱ ጥበቃና ልማት የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ከዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ሀብቱም ለጉዳት ተዳርጎ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመስሪያ ቤቱና በክልሎች ስር የሚተዳደሩ 25 ብሄራዊ ፓርኮች፣ ሁለት የእንስሳት መጠለያዎችና 80 የሚሆኑ ጥብቅ ቦታዎች ቢኖሩም በቂ መሰረተ ልማት ያልተዘረጋላቸው በመሆኑ ለቱሪዝም ዘርፉ ያስገኙት ጥቅም አናሳ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ልማቱን ወደ ሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች ለማስፋት ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡም በስፋትም ሆነ በብዝሃ ህይወት ሀብቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን የጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክ ያለበትን የመሰረተ ልማት ችግር ለማቃለልና ልማቱን ለማዘመን ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ኩመራ አስረድተዋል።
የጋምቤላ ክልል ባህላና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ፣ የጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክን ለማልማት የተጀመሩ ስራዎች ለክልሉ ቱሪዝም እድገት ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ፓርኩን ለማልማት ለተጀመረው ጥረት መሳካት ያልተቆጠበ የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን እንደሚያደርግ ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።