በታላቁ የረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መሥራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ የረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መሥራት አለበት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፡-በታላቁና የተከበረው የረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ክብርና ጽሞና የሚሰጠው የረመዳን ፆም ሊጀመር ቀናቶች ቀርተውታል።
በኢስላማዊ የጊዜ ቀመር በዘጠነኛው ወር ላይ በፆምና በተለየ መልኩ መልካም ሥራዎች የሚበዙበት የረመዳን ወር በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቅ መሆኑ ይታወቃል።
የረመዳን ወር ከንጋት እስከ ምሽት ከምግብና መጠጥ በመከልከል መልካም ተግባራትን በማብዛት ከፈጣሪ ምሕረት የሚለመንበት መሆኑም እንዲሁ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የታሪክና ቅርስ ዘርፍ ተጠሪ ሸኸ ሙሐመድ አሚን፤ በረመዳን የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት የእዝነት፣ ቀጣዮቹ አሥር ቀናት የምሕረት እና ቀሪዎቹ ቀናት ደግሞ ከእሳት ነፃ የሚሆኑበት መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም መጪውን የፆም ወቅት በአግባቡ ለመጠቀም ሕዝበ ሙስሊሙ መዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመው፤ በተከበረው ወር የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መሥራት ይገባናል ብለዋል።
የተከበረው የረመዳን ወር የተጣላ የሚታረቅበት፣ ከቂምና ጥላቻ በመራቅ ይቅርታ የሚደረግበት፣ ለመልካም ሥራ ከፈጣሪ ከፍ ያለ ዋጋ የሚገኝበት በመሆኑ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ሁላችንም እንዘጋጅ ብለዋል።
በኢስላማዊው አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር በሆነው የረመዷን ወር ለእምነቱ ተከታዮች መፆም ግዴታ የተደረገ መሆኑ ይታወቃል።