ቀጥታ፡

በሕዳሴ ግድብ 13ኛ ዓመት ክብረ በዓል የድጋፍ ማሰባሰብ ንቅናቄ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት 13ኛ ዓመት ክብረ በዓል የድጋፍ ማሰባሰብ ንቅናቄ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ አምስት በመቶ ብቻ ለቀረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ፍጻሜ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት መግለጫ ሰጥቷል።

13ኛው ዓመት ክብረ በዓል "በኅብረት ችለናል!" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ተገልጿል።

የፅሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር፤ የግድቡ አጠቃላይ አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን አብስረዋል።

ከዚህም ውስጥ የሲቪል ሥራው 98 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራው 78 በመቶ መድረሱን አንስተዋል። 

ፕሮጀክቱ የመላ ኢትዮጵያውያን የመግባባትና የከፍታ ምልክት መሆኑን ገልፀው፣ የመንግሥት ቁርጠኛ አቋምና የዲፕሎማሲ ጥረት እና የህዝቡ ድጋፍ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።

ግድቡ የይቻላል መንፈስን የፈነጠቀ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀው፤ በዚህም አሁን ላይ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እያመነጩ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ተርባይኖች እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ 13ኛ ዓመት በቦንድ ሽያጭ ሳምንት፣ በዐውደ-ርዕይ፣ በምስጋና፣ ዕውቅናና ሌሎች የድጋፍ ማሰባሰብ የንቅናቄ መድረኮች እንደሚከበር ተናግረዋል። 

ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን  በሕዝብ ተሳትፎ 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸው፥

በ13ኛ ዓመት የክብረ በዓል ንቅናቄ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዷል ነው ያሉት።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ መልዕክት ካስተላለፉ የህብረተሰብ ተወካዮች መካከል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ ሕዳሴ ግድብ እንደ አድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድል መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ ሕብረትና አንድነታችን የታየበት እና ብዙ ትምህርት የሰጠን ነው ያሉት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም፥ የነገ ምንዳ የሚሆን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

አሁን ለተደረሰበት ስኬት አሻራ ያሳረፉ አካላትን አመስግነው፥ በቀጣይም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ  የሁሉም ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ ግድቡ ኢትዮጵያዊያን በትልቅ ሞራልና ተነሳሽነት የገነቡት፣ በስስት የሚያዩትና ፍፃሜውን በጉጉት የሚጠብቁት  ነው ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን በራስ አቅም መለወጥ እንደሚቻል ያሳየ፣ የአንድነት አሻራ የታተመበትና ከድህነት መውጫ መንገድ እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁንም በጀመርንበት ልክ ድጋፋችንን በማጠናከር ለፍፃሜው ማብቃት ይገባል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ እና አቶ ጌታሁን ሁሴን፥ ለግድቡ ግንባታ ሂደት በዲፕሎማሲው መስክ ትላልቅ ስራዎች መሰራታቸውን አውስተዋል።


 

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ መጠናቀቅ ሚናቸውን እንዲያጎለብቱ ሚዲያ ተቋማትም የንቅናቄ ስራዎችን በስፋት እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በመወከል የተገኙት ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው፥ ፓርቲዎቹ ሕዳሴ ግድብን በመሰሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ በሁሉም መስክ ትልቅ ትርጉም ያለው ግድብ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም