ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለስደተኞች የዲጂታል መታወቂያ መስጠት ጀመረች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለስደተኞች የዲጂታል መታወቂያ መስጠት ጀመረ።

ተቋሙ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነው ዲጂታል መታወቂያውን መስጠት የጀመረው። 

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲከበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ ለስደተኞች የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም ስደተኞች በብሔራዊ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተቱ ያስችላል ብለዋል። 

ስደተኞች ዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኙ መደረጉ የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ያሉት ደግሞ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮዳሄ ዘሚካኤል ናቸው።


 

የዲጂታል መታወቂያ መኖሩ በተቋማት መካከል የተቀናጀና የተናበበ የስደተኞች መረጃ እንዲኖርና ይህም ስደተኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው ነው ያብራሩት። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው ምቦጎሪ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የዲጂታል መታወቂያ መስጠቷ ትልቅ እርምጃ ነው።  


 

ኢትዮጵያ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በብሔራዊ ሥርዓት ውስጥ በማካተት ከምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ አገር እንደሚያደርጋት ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣውን የስደተኞች መብትን በማክበር ረገድ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ መታወቂያው የሚፈልጉትን አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።  

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት የመጡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም