በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሀገሪቱ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ስራ ጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሀገሪቱ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ስራ ጀምረዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፡- በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በሀገሪቱ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ስራ መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 የሁለተኛው ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የግምገማው ሂደት ትኩረት ካደረገባቸው ኢኮኖሚያዊ መስኮች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ዘርፉ አፈጻጸም መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በተለያዩ ችግሮች ደካማ እንደነበር ጠቅሰው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በስፋት ወደ ምርት እንዲገቡ መደረጉን አስታውሰዋል።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተወሰዱ እርምጃዎች የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 56 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል።
ከፋይናንስ፣ ከጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ከሰው ኃይል፣ ከገበያ ትስስር፣ ከኤሌክትሪክና መሰል መሰረተ ልማቶች ማሟላት አኳያ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት የማምረት አቅም ማደጉን ተናግረዋል።
የፍጆታ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ለወጪ ንግድ ብቻ ሳይሆን ገቢ ምርት መተካት ላይ የተሰጠው ትኩረት በግምግማው በአዎንታዊ አፈጻጸም መነሳቱን ጠቅሰዋል።
በበጀት አመቱ ስድስት ወራት በተኪ ምርት 1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 994 ሚሊዮን ዶላር መሳካቱን ጠቅሰው አፈጻጸሙም 93 በመቶ መሆኑን አንስተዋል።
በግማሽ ዓመቱ 67 የውጭ ባለሀብቶችን በኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 127 ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።
ከሀገር ውስጥ ደግሞ 2 ሺህ 300 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት ታቅዶ 1 ሺህ 490 ያህል ወደ ዘርፉ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ከመሰማራት ባለፈ ባለፉት ስድስት ወራት የውጭና ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ በተሰራው ስራ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለ142 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ121 ሺህ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።
በመድረኩ ከተዳሰሱ የዘርፉ ተግባራት መካከል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈጻጸም ይገኝበታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ንቅናቄው ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱን ሀብት በማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ በመስጠት፣ ለኢንቨስትመንት ምች ሁኔታ በመፍጠር፣ የቅንጅት ችግሮችን በመፍታት፣ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ረገድ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው በሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት፣ የመንግስት ግዥ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲስተካከል፣ መሰረተ ልማትን ጨምሮ ምቹ ሁኔታ የመስጠት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
ከወጪ ንግድ አኳያ ዘርፉ ያለው ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዲያድግ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።