የቡድን ሥራ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል- አትሌቶችና የቡድን መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የቡድን ሥራ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል- አትሌቶችና የቡድን መሪዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፦በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እና በስድስተኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የነበረው የቡድን ሥራ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን አትሌቶችና የቡድን መሪዎች ገለጹ።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እና በስድስተኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድኖች ትናንት የእውቅና መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
በስኮትላንድ በተካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅ፣ በአንድ የብርና በአንድ የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በቱኒዚያ በተካሄደው ስድስተኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅ፣ አምስት የብር እና ሦስት የነሐስ በድምሩ አሥር ሜዳሊያዎች በመያዝ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።
በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ፅጌ ድጉማ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ታሪክ በርቀቱ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቷ ደስታን እንደፈጠረባት ገልጻለች።
ለሻምፒዮናው ጥሩ ዝግጅት ማድረጓንና በግሏ የነበራት የራስ መተመማን ውድድሩን እንድታሸንፍ እንዳደረጋት ተናግራለች።
በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በመሳተፍ ውጤት ለማስመዝገብ እንደምትፈልግ ነው የገለፀችው።
በሻምፒዮናው በ1 ሺህ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ፤ በውድድሩ ላይ የነበረው የቡድን ሥራ ውጤቱ እንዲገኝ አድርጓል ብላለች።
የስድስተኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን መሪ ናስር ሁሴን በበኩሉ፤ በውድድሩ ፈታኝ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም አትሌቶቹ ጫናውን በመቋቋም መልካም ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጿል።
በተለይም በተስፈኛ አትሌቶች የተገኘው ውጤት በተተኪ አትሌቶች ላይ በይበልጥ ከተሰራ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተናግሯል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም መድረኮች የአገራቸውን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው የሚያስጠሩ ናቸው።
በቱኒዚያና ስኮትላንድ የተመዘገቡት ውጤቶች አትሌቶች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው አገር የሰጠቻቸውን አደራ መወጣት እንደሚችሉ ያሳዩ ናቸው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ አትሌቶች የአሸናፊነትና የፅናት ተምሳሌት እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
በቀጣይ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተፎካካሪዎች በልጦ ለመገኘትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል።
መንግሥት ኢትዮጵያ በቀጣይ በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስፖርታዊ መድረኮች የተሻለ ውጤት እንድታገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሮቹ አመርቂ ውጤት በማስመዝገባችሁ ኢትዮጵያ ኮርታባችኋለች ብለዋል።
ውጤቶቹ አበረታች ቢሆኑም በፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችና በቀጣይ በሚከናወኑ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ብዙ መሥራት እንደሚገባ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስ ስፖርት ለመሳተፍ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ ዳዊት አስፋው፤ በውድድሮቹ ላይ የተገኙት ወጤቶች በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታ ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለአትሌቲክሱ ስፖርት እድገት ድጋፉን ማድረግ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ለልዑካን ቡድኑ አባላት በአጠቃላይ ከ800 ሺህ ብር በላይ ሽልማት አበርክቷል።