የጤና አገልግሎትን ማዘመንና ጥራት ማስጠበቅ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎትን ማዘመንና ጥራት ማስጠበቅ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2016(ኢዜአ)፦የጤና አገልግሎትን ማዘመንና ጥራት ማስጠበቅ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ተናገሩ።
8ኛው ሀገር አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባኤ በአዲስ አበባ አፍሪካ ኀብረት አዳራሽ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ከጉባኤው ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ በጤና አገልግሎት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችና ስኬቶችን የሚያስቃኝ አውደ ርዕይም የተከፈተ ሲሆን በጉባኤው ተሳታፊዎች ተጎብኝቷል።
በጉባኤው የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች፣ የፌደራልና ክልል ጤናው ዘርፍ ተወካዮች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትና ለጋሾች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾሞ፤ በጤናው መስክ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል ሥርዓት ከጤና ኤክስቴሽን ለውጥ ተግባራት ጋር ተዳምሮ ስኬታማ እንቅስቃሴ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የእናቶችና ህጻናትን ሞት በመቀነስ፣ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት እንዲሁም በህክምና ጥራት ላይ የተገኙ ስኬቶች ማሳያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የኤሌክትሮኒክ ጤና መረጃ ስርዓትም በጤና ተቋማት ገቢራዊ መደረጉን አስታውሰው በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ውጤታማ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
በጤና አገልግሎት ረገድ አበረታች ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ አዲስ ዓይነት አሰራር መከተል ይገባል ብለዋል።
በጤናው መስክ የተገኙ ስኬቶችን በማጎልበት የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከምንግዜውም በላይ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
የጤና አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ፈጠራን ማበረታታት፣ በቂ ኃብት መመደብና ትኩረት መስጠት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ሚኒስቴሩ በትብብር እየሰራ ነው።
በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሰው ኃይል አቅም ግንባታ በኩልም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር ቢጆይ ናምቢያር፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ጥራትን እንዲሁም ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ በጤናው ዙሪያ ለማሳካት የተያዙ ግቦች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
ጉባኤው ከየካቲት 26 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።