ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ 20 የሚደርሱ ቦይንግ 777ኤክስ 9 አውሮፕላኖችን ሊገዛ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፍሪካ በአይነታቸው የመጀመሪያ የሆኑ 20 ቦይንግ 777 ኤክስ 9 የተሰኙ ግዙፍ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ የመግባቢያ ስምምነት አደርጓል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳና የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አርቭን ሆሴ ማሲንጋና የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች ተገኝተዋል::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ይህ አውሮፕላን በግዙፍነቱና በአይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው።

ትዕዛዝ ከተፈፀመባቸው 20 የቦይንግ 777 ኤክስ 9 አውሮፕላኖች መካከል ስምንቱን እ.አ.አ እስከ 2030 አየር መንገዱ የሚረከብ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም 3ቱ በ2027 3ቱ በ2029 እንዲሁም 2ቱ በ 2030 የሚረከቡ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

ይህ ግዙፍ አውሮፕላን እያንዳንዱ 440 መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን 15 የቢዝነስ ክፍል መቀመጫ እንዳለውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ህዳር ወር 2016 ዓ.ም በቅርቡ ከቦይንግና ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያዎች በድምሩ 84 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ለመግዛት ሥምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

በተጨማሪም በጥናት ላይ የተመሰረተ ተመሳሳይ የአውሮፕላን ትዕዛዞችን ለማድረግ መታቀዱንም ገልጾ ነበር።

ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን እድገትን በመከተል ዓለም ላይ ካሉ 20 ምርጥ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም