ቀጥታ፡

ለመቀሌ ፊዚዮቴራፒ ማዕከል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ ተደረገ

መቀሌ ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦ለመቀሌ ፊዚዮቴራፒ ማዕከል የ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ቁሶች ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረገው በጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል ነው።

የማዕከሉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ደምስ ይሄይስ ዛሬ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው።

"እውቀትና ክህሎት ያላቸው አካል ጉዳተኞች አምራችና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ያሉት ዶክተር ደምስ፣ ለእዚህም የጤና ተቋማት ተባብረው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለማዕከሉ በተደረገው ድጋፍ ሰው ሰራሽ እግር እና እጅ እንዲሁም ለሕክምና አገልግሎት የሚሆኑ ቁሶች መካተታቸውን ገልጸዋል።

ማዕከሉ የጀመረውን ድጋፍ በቀጣይም እንደሚያጠናክርና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አማኑኤል ሃይለ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ የሚፈልጉ በርካታ አካል ጉዳተኞች አሉ።

ማዕከሉ ላደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ አመስግነው እንደዚህ አይነት ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ 25 አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ድጋፉም ለረጅም ዓመታት የሚያገለግል መሆኑን ገልጿል።

የሰው ሰራሽ እግር ድጋፍ ያገኘው ወጣት ረዳኢ ተስፋይ ድጋፉ በተሻለ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ስላስቻለው ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም