የጤፍ ምርታማነትን የሚጨምር የ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር የጥናትና ምርምር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የጤፍ ምርታማነትን የሚጨምር የ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር የጥናትና ምርምር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2016(ኢዜአ)፦የጤፍ ምርት ምርታማነትን የሚጨምር የ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር የጥናትና ምርምር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።
ጥናትና ምርምሩን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከዶናልድ ዳንፎርዝ የዕጽዋት ሳይንስ ማዕከል በጋራ የሚያካሂዱት ሲሆን፤ የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ጥናትና ምርምሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የጤፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮ-ቴክኖሎጂ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ግርማ፤ በዘረመል አርትዖት አማካኝነት የጤፍ አዝዕርት እንዳይጋሽብ የሚያደርግ ጥናትና ምርምር የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምርምሩ ግሽበትን የሚቋቋም የጤፍ ዝርያዎችን በማባዛት የዘረመል አርትዖትን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸው፤ ለአርሶ አደሩ ግሽበትን የሚቋቋምና ምርታማነቱ ከፍያለ ዝርያ ተደራሽ ማድረግ የምርምሩ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡
በጤፍ አዝዕርት መጋሸብ ከ20 እስከ 30 በመቶ የምርት ብክነት ይከሰታል ያሉት ዶክተሩ የሚካሄደው ምርምር ይህን የሚያስቀር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ምርምሩ የጤፍ ምርትን ሜካናይዝድ በሆነ መንገድ ለማጨድ የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ከመሠረቱ የሚፈታ መሆኑን ገልጸው፤ ለአራት ዓመታት የሚካሄደው ምርምር ጤፍን በማጨጃ ማሽኖች ማጨድ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በዶናልድ ዳንፎርዝ የዕጽዋት ሳይንስ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ጌቱ በየነ፤ በአሜሪካ ሀገር በተደረገ ምርምር የጤፍ አዝዕርት የግሽበት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያም ሁለቱ ተቋማት በግብርና ምርምር ማዕከላት የጤፍ ግሽበትን የሚቋቋም የጤፍ ዘር ለማባዛት እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጤፍ ምርትን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በጤፍ ላይ የተለያዩ ምርምሮችን ያካሄዱት እና ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ክበበው አሰፋ በበኩላቸው፤ ምርምሩ ከ20 እስከ 30 በመቶ የነበረውን የምርት ብክነት የሚቀንስ ስለመሆኑ አንስተዋል።
አሁን ላይ ያሉትን ምርጥ ዘሮች በማዳቀልና ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል ከፍተኛ ምርት ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በአንድ ሄክታር በአማካይ 24 ኩንታል ሲመረት፤ ከፍተኛው ደግሞ 28 ኩንታል መሆኑን ጠቁመው፤ ምርምሩ ምርታማነትን በመጨመርና በ2030 በሄክታር 30 ኩንታል ምርት ለማድረስ የተያዘውን ግብ የሚያሳካ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡